በዝዋይ የሚታየው ከፍተኛ የውሃ እጥረት እንደቀጠለ ነው

መጋቢት ፰ (ስምንት)ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የዝዋይ ሃይቅ ሼር በሚባለው የሆላንድ አበባ እርሻ በሚለቀው አደገኛ ኬሚካል የተነሳ፣ ህዝቡ ከሃይቁ ተጣርቶ የሚመጣውን ውሃ መጠቀም ካቆመ ሳምንታት ቢቆጠሩም፣ የኦሮምያ ክልል ባለስልጣናት መፍትሄ ሊሰጡት አልቻሉም። የአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚሉት ባለስልጣናት ህዝቡ ከሃይቁ የሚመጣውን የቧንቧ ውሃ እንዳይጠቀም ቢከለክሉም፣ አማራጭ መፍትሄ ግን አላስቀመጡም። የከተማው ህዝብ ከከተማው ውጭ በመኪና እየተጫነ የሚመጣለትን ውሃ እየገዛ ለመጠቀም ተገዷል።
የውሃው ችግር ተባብሶ በቀጠለበት ሰአት፣ የሃይቁ አሳዎችም እየሞቱ ነው። ፖሊሶች አሳ አስጋሪዎች አሳዎችን እንዳያጠምዱ ክልከላ እያደረጉ ነው። ውሃ ከሃይቁ የሚስቡ እጽዋትም መልካቸው ወደ ቢጫነት እየተለወጠና እየደረቁ መሆናቸውን ነዋሪዎች ይናገራሉ።
የገዢው ፓርቲ ባለስልጣናት ሼር ኢትዮጵያ ወደ ሃይቁ የሚለቀውን ኬሚካል እንዲያቆም ባለማስደረጋቸው ችግሩ ተባብሶ እንዲቀጥል አድርጎታል።