በዛሬው የጁመዓ ጸሎት ሙስሊሞች በዝምታ ተቃውሞአቸውን አካሂደው በሰላም ተበትነዋል

ጥቅምት ፪ (ሁለት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በዛሬው የጁመዓ ጸሎት የስግደት መርሀ ግብር ላይ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች በአዲስ አበባ መርካቶ አንዋር መስጊድ በዝምታ ተቃውሞአቸውን አካሂደው በሰላም ተበትነዋል

ዛሬ ከቀኑ 4፡30 ጀምሮ በአንዋር መስጊድ እና በአካባቢው ከፍተና ቁጥር ያላቸው የመንግስት የደህንነት ሀይሎች በአለባበስ ሙስሊም መስለው መቀላቀላቸውን ለዘጋቢአችን የገለጡት አንድ የመስጊድ አስተናጋጅ፣ የፌደራል ፖሊሶች ዝግጁ ሆነው በኡመር ሰመተር ትምህርት ቤት እና በአራተኛ ፖሊስ ጣቢያ ተከማችተው ነበር ብለዋል።
በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የአዲስ አበባ እና የአካባቢው ሙስሊም ኢትዮጵያውያን ተሰብስበው የሰገዱ ሲሆን ከስግደት በሁዋላ በመቀመጥ የዝምታ ተቃውሞ አድርገዋል።

ባለፈው እሁድ የተካሄደውን የመጅሊስ ምርጫ ተከትሎ መንግስት፣ ከእንግዲህ ወዲያ ማንኛውም ተቃውሞ ቢነሳ የሀይል እርምጃ ለመውሰድ እቅድ እንዳለው በመታወቁ ነው በዛሬው እለት በአንዋር መስኪድ የዝምታ ተቃውሞ የተካሄደው። የኢሳት የድምጻችን ይሰማ ምንጮች እንደገለጡት፣ መንግስት ሙስሊሙ ማህበረሰብ መሪውን የመረጠ በመሆኑ፣ ከእንግዲህ ወዲያ መሪዎቻችንን በነጻ ምርጫ እንምረጥ በማለት ለተቃውሞ የሚወጡትን ለመምታት ዝግጅት በማድረጉ ሙስሊሙ ማህበረሰብ ከእንግዲህ ወዲያ ስለሚወስደው የተቃውሞ እንቅስቃሴ በመምከር ላይ ነው።

ዘጋቢያችን ያነጋገራቸው አንድ የድምጻችን ይሰማ ተቃውሞ አስተባባሪ እንደገለጹት ባለፈው ለኢህአዴግ መንግስት የማስጠንቀቂያ ቢጫ ካርድ የመዘዝን ስለሆነ ሁኔታዎችን ካላሻሻለ ደግሞ ቀጣዩ የመጨረሻ ቀይ ካርድ ይሆናል ብለዋል። ግለሰቡ እንዳሉት በመጪው የአረፋ በአል ላይ ከፍተኛ ተቃውሞ ለማድረግም ዝግጅታችንን እያጠናቀቅን ሲሆን አሁን የዝምታ ተቃውሞውን መንግስት በጥሞና ወስዶ ከስህተቱ ይታረማል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጠዋል።

በአንጻሩ በክልሎች በተለይም በበደሌ ከፍተና ታቀውሞ እንደነበርና ምእመናንም በፖሊሶች ቁጥጥር ስር እንደዋሉ ለማወቅ ተችሎኦል።

በተመሳሳይ ዜናም የሙስሊሙ መሪዎች በትናንትናው እለት አራዳ በሚገኘው የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ቢቀርቡም ለጥቅምት 15 ቀን 2005 ዓም ቀጠሮ የጊዜ ቀጠሮ ተሰጥቶአቸው ወደ እስር ቤት ተመልሰዋል።