በዋካ የተነሳውን ግጭት ተከትሎ የቶጫ ወረዳ አስተዳዳሪ የህዝቡ ጥያቄ ፍትሀዊ ሆኖ እያለ እኛ ግን እስከዛሬ ስናፍነው ነበር በማለት ስልጣናቸውን ለቀቁ

ህዳር 1 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና:- በዋካ የተነሳውን ግጭት ተከትሎ የቶጫ ወረዳ አስተዳዳሪ የህዝቡ ጥያቄ ፍትሀዊ ሆኖ እያለ እኛ ግን እስከዛሬ ስናፍነው ቆይተናል፣ ከእናንተ ጋር ከእንግዲህ አልሰራም በማለት ስልጣናቸውን ለቀቁ

የኢሳት የደቡብ ወኪል እንደገለጠው አስተዳዳሪው አቶ ፈቃዱ ወልደ ሩፋኤል “የህዝቡ ጥያቄ ፍትሃዊ ሆኖ እያለ፣  እኛ ግን ጥያቄውን ለማፈን በተደጋጋሚ ሙከራ አድርገናል” በማለት
ስልጣናቸውን በፈቃዳቸው ለቀዋል።

እርሳቸውን ተከትለው ሌለው ስልጣን የለቀቁት ደግሞ አቶ ከበደ ካሳ የተባሉት የዞኑ አቃቢ ህግ ሲሆኑ እርሳቸውም ለመልቀቂያቸው ተመሳሳይ ምክንያት አቅርበዋል።

ህዝቡን እንደተሳደበና እንዳስፈራራ የተነገረለት የጸጥታና ፍትህ ዘርፍ ሀላፊው አቶ ተሜሳ፣ የስልጣን መልቀቂያ ደብዳቤ ቢያስገባም፣  ሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣኖች መልቀቂያውን አንቀበልም ብለውታል።

ባለስልጣኖቹ ለአገር ሽማግሌዎች ” ይኸው እናንተን የሰደበው ሰው ስልጣን ልልቀቅ ሲል አንቀበልም ብለነዋል።” በማለት እንደነገሩዋቸው ከሽማግሌዎቹ አንዱ ለኢሳት ገልጠዋል።

በተያያዘ ዜናም የአካባቢው ባለስልጣናት ለኢሳት መረጃ የሰጡት ሰዎችን ለማግኘት ሲሉ በርካታ ወጣቶችን ማሰራቸውን ለማወቅ ተችሎአል። የአካባቢው ሰዎች እንደሚሉት በወረዳው ያለው ውጥረት አሁንም እንደቀጠለ ነው። በዋካ ከተማ በተነሳው ተቃውሞ በርካታ የአግር ሽማግሌዎች ታስረው መለቀቃቸው ይታወሳል።