በዋካ ከተማ የተነሳውን ህዝባዊ ተቃውሞ መርተዋል የተባሉት አባት ከሀላፊነት እንዲነሱ ተደረገ፣ ህዝቡ ግን ተቃውሞውን እያሰማ ነው

ህዳር 6 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በአካባቢው ያለውን ጭቆና፣ የመልካም አስተዳዳርና የፍትህ መታጣት በመቃወም እራሱን በእሳት በማጋየት ተቃውሞን የገለጠው የመምህር የኔሰው ገብሬ አስደንጋጭ ዜና የህዝቡ የመነጋገሪያ አጀንዳ በሆነበት ማግስት፣ የአካባቢው የሀይማኖት ባለስልጣናት፣ “ተቃውሞውን የሚያስተባብሩት በከተማው የሚገኘው የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ካህን ናቸው”  በሚል ሰበብ  ፣ የቤተክርስቲያኑዋን አስተዳዳሪ የሆኑትን በኩረ ትጉሀን ይልማ መኮንንን ከሃላፊነት አንስተዋል።

የእገዳውን  ደብዳቤ የጻፉት የዞኑ የአገረስብከት ሀላፊ የሆኑት መምህር ወንዶሰን ክፍሌ ሲሆኑ፣ ለበኩረ ትጉሀኑ ከሀላፊነት መነሳት ምክንያት አድርገው ያቀረቡት “ሀይማኖትን ምክንያት በማድረግ መንግስትና ህዝብ እንዲጋጩ አድርገዋል” የሚል ነው።

በቁጥር ዳ/ ካሲ/ 322/ 2004፣ በቀን 24-02-2004 ለበኩረ ትጉሀን ይልማ መኮንን ከስራ እና ከደሞዝ መታገዳቸውን ስለማሳወቅ በሚል ርእስ በተጻፈው ደብዳቤ የሚከተለው ይዘት ሰፍሯል።

” ግለሰቡ በመንግስታዊ ወይም ፖለቲካ አሰራር ጣልቃ ከመግባታቸውም በተጨማሪ ጉዳዩን ሀይማኖታዊ ሽፋን በመስጠት ህዝቡን እና ቤተክርስቲያንን ከመንግስት ጋር ለማጋጨት ከፍተኛ ጥረት ከማድረጋቸውም በላይ የአንድ ሀይማኖት መሪ የሆነ ሰው የአካባቢውን ሰላምና አንድነትን የማስጠበቅ ሀላፊነቱን ወደ ጎን በመተው  የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የአገሪቱን ሰላምን፣ ጸጥታን እንዲሁም የልማት አጋር በመሆን የነበራትን መልካም ስም እና ዝናን በአካባቢው ጥላሸት እንዲቀባ አድርገዋል፣ ስለሆነም ይህን ጉዳይ እጅግ ከፍተኛ ትኩረት የምንሰጠው በመሆኑ ሀይማኖታዊ ፖለቲካ ስለማይኖረን አገረስብከቱ አስፈላጊውን ማጣሪያ አድርጎ ውሳኔ እስከሚሰጥበት ድረስ ከቀን 24-02-2004 ጀምሮ ከስራ ሀላፊነት ከማንኛውም አገልግሎትና ከደሞዝ የታገዱ መሆናቸውን እያስታወቅን የንብረት ርክክብ በቦታው ላለው ካህን እንዲፈጸም ሆኖ ከዛሬ ጀምሮ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንን እንዳይወክሉ ለሁሉም አካላት በጥብቅ እናስታውቃለን”

እገዳውን ተከትሎ የአካባቢው ፖሊስ ባለፈው እሁድ ወደ ቤተክርስቲያኑዋ በመሄድ መምህር ይልማ ንብረት እንዲያስረክቡ ሲጠይቁ፣ ህዝቡ “መንግስት በቤተክርስቲያናችን ውስጥ ምን አገባው፣ ሰበካ ጉባኤያችን እያለ የመንግስት ባለስልጣናት በሰጡት ትእዛዝ ደረጃውን ያልጠበቀ እገዳ ተደርጓል፣ የቤተክርስቲያናችን መብት ተረግጧል፤ አቶ ተፈራ ታደሰ የተባሉ የቤተክርስቲያናችን ተከታይ ጥቅምት 14   ከቤተክርስቲያኒቱ
ግቢ በፖሊስ ታፍነው ሲወሰዱና የቤተክርስቲያኑዋ ህልውና ሲነካ ያልተከላከሉ ሀላፊዎች፣ ቤትክርስቲያናችን እንደትዘጋ ማድረጉ በጣም ያሳዝናል” በማለት ተቃውሞአቸውን አሰምተዋል።

የህዝቡ ተቃውሞ ያሰጋው ፖሊስ በአካባቢው የፖሊስ ሀይል እንዲጨምር ባደረገበት ወቅት፣ ሻምበል ዮሀንስ አስራት የተባሉ የወረዳው የደህንነት ሹም  ለፖሊሶቹ ” ይሄ የሚደረገው ነገር ህገ ወጥ ነው፤ በቤተክርስቲያን ጉዳይ ላይ ፖሊስን ምን አገባው፣ ካህኑ በሶስት ማስረጃ ወንጀል መፈጸማቸው እስካልተረጋገጠ ድረስ ፖሊስ ሊይዛቸው ስለማይቻል እኔ በዚህ ጉዳይ እጄን አላስገባም፣ አንድም ካህን በፖሊስ ተይዞአል ተብሎ እንዳልሰማ በማለቱ” በስፍራው የነበሩት ፖሊሶች ተበትነዋል።

የመንግስት ባለስልጣናት እርስ በርሳቸው መወዛገባቸውን የሚገልጡት የአካባቢው ሰዎች፣ የአካባቢው ህዝብ ግን አሁንም ቤተክርስቲያኑዋን በአንክሮ እየጠበቀ መሆኑ ታውቋል። መምህር ይልማ በወረዳው ህዝብ ተመርጠው የወረዳውን ችግር ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ለማቅረብ ከተላኩት የአገር ሽማግሌዎች መካከል አንዱ ናቸው።

በጉዳዩ ዙሪያ የአካባቢውን ባለስልጣናት ለማግኘት ተደጋጋሚ ሙከራ ብናደርግም አልተሳካልንም። ከመምህር የኔሰው ገብሬ ሞት በሁዋላ የአካባቢው ወጣቶችን መረጃዎችን ለውጭ አገር የመገናኛ ብዙሀን ሰጥታችሁዋል በሚል እየተዋከቡ መሆናቸው ታውቋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የቢቢሲን የምርመራ ጋዜጠኝነትን ቢሮ ጨምሮ ሌሎች የአለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሀን የመምህር የኔሰው ገብሬን አሟሟት ሰፊ የዜና ሽፋን እየሰጡት ነው

የኢትዮጵያ መንግስት እስካሁን በዋካ ለተፈጠረው ችግር በቂ መልስ አልሰጠም።