በዋልድባ ገዳም አቅራቢያ በአማራና በትግራይ ሚሊሺያዎች መካከል የተጀመረው ግጭት መቀጠሉ ተገለጸ

ኢሳት ( መጋቢት 27 ፥ 2009)

በዋልድባ ገዳም አቅራቢያ በአማራና በትግራይ ሚሊሺያዎች መካከል ትናንት የተጀመረው ግጭት መቀጠሉን የአካባቢው ምንጮች ለኢሳት ገለጹ።

ለንግስ አምበርታት ገዳም የነበሩ ምዕመናን በግጭቱ ከጉዟቸው መገታታቸው ታውቋል። በዋልድባ አምበርታት ገዳም መጋቢት 27 ፥ 2009 በሚከበረው የመድሃኒያለም ክብረ በዓል ላይ ለመገኘት ይጓዙ የነበሩ የአማራ ክልል ሚሊሺያዎች ትጥቃቸው እንዲፈቱ በመጠየቃቸው ማክሰኞ ዕለት በተጀመረው ግጭት ከሁለቱ ወገን 6 ሚሊሺያዎች ተገድለዋል።

በአካባቢው በሚሊሺያዎች መካከል የተፈጠረው ግጭት አመታዊ በዓሉን ባያስተጓጉልም፣ ከንግስት የሚመለሱ ሰዎች መታገታቸውን ግን ለማወቅ ተችሏል።

ግጭቱ ረቡዕ ዕለት መጋቢት 27 ፥ 2009 አም የቀጠለው ዋልድባ ገዳም አካባቢ እምብርት በተባለ ተራራ ላይ ሲሆን፣ በትግራይ ሚሊሺያዎች በኩል የመከላከያ ሰራዊት አባላት ተሳታፊ ስለመሆናቸው እየተነገረ ሲሆን፣ ከካላሽንኮቭ ጠብመንጃ ያለፈ የመትረየስ ተኩስ መሰማቱ መከላከያ ሰራዊት ተሳትፏል የሚል ግምት ማሳደሩን ምንጮች ለኢሳት ገልጸዋል።