በወጣቶች እንቅስቃሴና በሰብኣዊ መብት ረገጣ የአንድ ወር ሪፖርት ቀረበ

መጋቢት ፲፩ (አስራ አንድ) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-እኤአ ከየካቲት 9 እስከ መጋቢት 9/2012 በክልሉ ዉስጥ ስለነበረዉ የወጣቶች እንቅስቃሴና በመንግስት በኩል ስለተወሰደዉ የመብት ረገጣ የሚገልፀዉን የአንድ ወር ዝርዝር ሪፖርት ያወጣዉ የኦሮሚያ ወጣቶች ንቅናቄ  የተባለዉ ድርጅት ነዉ።

በመንግሰት ጥቃት የተፈፀመባቸዉን የኦሮሞ ተወላጆች በሙሉ በስም በመጥቀስ ድርጅቱ ባወጣዉ ሪፖርት፤ በኦሮሚያ  ምእራብ ሸዋ ዞን በአዳ-በርጋ ወረዳ አነስተኛ ገበሬዎችን ከመሬታቸዉ በማፈናቀል ከኢትዮጵያ መንግሰት ጋር ተመሳጥሯል የተባለ አንድ የቻይና ኢንቬስተር መገደሉን፤ በኢሉ አባቦራ ዞን በዴሌ አላባሽ አካባቢ ለ1200 ነዋሪዎች መፈናቀል ምክንያት ነዉ የተባለ ፓኪስታናዊ  በ15ሺህ ሄክታር ላይ የተተከለ የሸንኮራ አገዳ ተክል በአንድ ሳምንት ልዩነት ሁለት ጊዜ በእሳት መጋየቱን ገልጧል።

በምስራቅ ሸዋ ዞን አዲስ የተገነባው ኩሪፍቱ መዝናኛ መጋቢት 8 ቀን 2012 ባልታወቁ ሰዎች መቃጠሉን በተጨማሪ ገልጦ  የቃጠሎዉ ምክንያት በአካባቢዉ የኦሮሞ ድሃ አርሶ አደሮችን ያለፈቃዳቸዉና ያለ ካሳ ከርስታቸዉ በማፈናቀል በሚደረገዉ ህገወጥ ተግባር ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ጠቁሟል።

ከዚህ በተጨማሪ በክልሉ ዉስጥ በሚገኙ ዩኒቨርስቲዎችና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጂማ፤ ድሬዳዋ ፤ ፊንፊኔ/ አዲስ አበባ ፤አዳማ፤ ነቀምት እና ሌሎችም ስፍራዎች እንዲሁም በሃዋሳ በሚገኙ በርካታ ቁጥር ያላቸዉ የኦሮሞ ተማሪዎችና ሲቪል ሰራተኞች ላይ መንግስት እስራትና ድብደባ ፈፅሞባቸዋል።

የኦሮሚያ ወጣቶች ንቅናቄ ባወጣዉ በዚህ ሪፖርት ቡርቃ ጃለላ የተባለ የኦሮሚኛ መፅሃፍ ደራሲና የአዳማ ዩኒቨርስቲ የ2ኛ አመት ተማሪ የሆነዉ ጫላ ሃይሉ ፤ በጂማ ዩኒቨርስቲ በተደረገ የተቃዉሞ ሰላማዊ ሰልፍ ተሳትፋችሁዋል የተባሉ 4 ወንዶችና 2 ሴት ተማሪዎች እንዲሁም ከምእራብ ሸዋ አምቦ ሁለት ተማሪዎች በመንግሰት የፀጥታ ሃይሎች ታፍነዉ የተወሰዱ ሲሆን ወጣቶቹ እስካሁን የት እንደደረሱ እንደማይታወቅና በተመሰሳይ ሁኔታ ዋቅጂራ ጉተማ የተባለ የአዳማ ዩኒቨርስቲ ተማሪ ከእስር ከተፈታ በሁዋላ የት እንደደረሰ እንደማይታወቅ ገልጿል።

ከጂማ ዩኒቨርስቲ  በሽብርተኝነት ወንጀል የተከሰሱ 20 የሚሆኑ ተማሪዎች፤ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ 14 እንዲሁም ፤ ከፊንፊኔ፤ ከምእራብ ሸዋ፤ ከሃረርጌ፤ ከአርሲ፤ ከምስራቅ ወለጋ 9 ተማሪዎች በእስር ቤት ግርፋትና ደብደባ እንደተፈፀመባቸዉና ታፍኖ ወደ ማእከላዊ እስር ቤት የተወሰደ ሚልኬሳ ሚዴቅሳ የተባለዉን የድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር ጨምሮ በምእራብ ሸዋ አዳበርጋ፤ ግንደበረት፤ ጀልዱና ሰበታ፤ በምስራቅ ወለጋ ነቀምትና ጊዳ አያና ጥቂት የማይባሉ የኦሮሞ ተወላጆች በእስር ላይ እንደሚገኙ ድርጅቱ አስታዉቋል።

4 የጂማ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ሙሉ በሙሉ ከትምህርት ገበታ መሰረዛቸዉንና 2 ተማሪዎች ደግሞ ለሁለት አመታት ያህል ከትምህርታቸዉ መታገዳቸዉን የኦሮሚያ ወጣቶች  ባቀረበዉ የአንድ ወር ሪፖርት አመልክቷል። 

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide