በኬንያ የሚገኘው የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኮሚሽን ቢሮ ሰራተኞች ጉቦና የወሲብ ጥያቄ ለመደለያ ይጠይቃሉ ተባለ

(ኢሳት ዜና–ጥቅምት 1/2010)በኬንያ የሚገኘው የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኮሚሽን ቢሮ ሰራተኞች ጉቦና የወሲብ ጥያቄ ለመደለያ ይጠይቁናል ሲሉ በሀገሪቱ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የፖለቲካ ስደተኞች አማረሩ።

ስደተኞቹ እንደሚሉት ጉቦ ሳይጨመርበት የስደተኛ ማመልከቻውን ለኮሚሽኑ ያስገባ ስደተኛ ሰራተኞቹ ማንነቱን አጋልጠው ችግር ውስጥ ሊወድቅ ይችላል።

ዘ ስታር የተባለው የኬንያ ጋዜጣ ባወጣው ሰፊ ዘገባ የኮሚሽኑ ሰራተኞች የኢትዮጵያውያኑን የስደተኝነት ጥያቄ ለማቀላጠፍ ጉቦ እንደሚጠይቁ በተለይም ሴቶቹ የወሲብ ጥያቄ እንደሚቀርባላቸው ካለዛ ግን ጉዳያቸው እንደሚስተጓጎል ተናግረዋል።

ጋዜጣው እውነተኛ ስሙን ለደህንነቱ ሲል ደብቆ ሰሚህ ብሎ የጠራው ግለሰብ እንደተናገረው ጉቦ ሳይጨምርበት የስደተኛ ማመልከቻውን ለኮሚሽኑ ካስገባ ሰራተኞቹ ማንነቱን አጋልጠው ችግር ውስጥ ሊወድቅ እንደሚችል ስጋት እንዳደረበት ተናግሯል።

በሀገሪቱ በብዛት የሚገኙት የሕወሃት የጸጥታ ሃይሎች እዛ እንደሚገኝ ካወቁ በመቶ የሚቆጠሩ ስደተኞች እጣ ሊገጥመው እንደሚችል ይህም ታፍኖ ወደ ኢትዮጵያ መመለስና በእስርና እንግልት መማቀቅ እንደሆነ ተናግሯል።

ግለሰቡ ጨምሮ እንደተናገረው ከኦሮሞዎች ጋር ግንኙነት አላቸው የሚባሉ የኬንያ ዜጎች እንኳ ከሕወሃት የደህንነት ሃይሎች እንደሚያመልጡ ተናግሯል።

እሱ በስም የሚያውቃቸው ሁለት ኬንያውያን ዋሪዎ ታቴሳና ጃልዴሳ ዋኮ የተባሉ በደህንነት ሃይሎች ከኬንያ ታፍነው ወደ ኢትዮጵያ ተወስደው የ15 አመት እስር ተፈርዶባቸዋል ብሏል።

ሪፖርቱ ሲቀጥልም በተለይ በሴቶች ላይ የሚደርሰው ችግር እጅግ የከፋ እንደሆነ ጠቅሶ ወሲብን በስጦታ የማያቀርቡ ሴቶች የስደተኛ ጥያቄያቸው ተቀባይነት እንደማያገኝ፣ቢመዘገቡ እንኳ ጉዳያቸው እንደሚጓተት ሜሎት የተባለች ስደተኛን ጠቅሶ አስነብቧል።

ሜሎት እንዳለችው የቀረበላትን የወሲብ ጥያቄ ባለመቀበሏ ካለምንም ወረቀት እንደምትኖር ነገር ግን እሷ የምታውቃቸውና ሴትነታቸውን በጉቦ መልክ ያቀረቡ ስደተኞች ጥያቄያቸው ተቀላጥፎ አሁን በምዕራቡ አለም ይኖራሉ ብላለች።

ከሀገሬ ሸሽቼ የወጣሁት የነጻነት አየር ለመተንፈስና ማንነቴን ለማስከበር ነበር።እዚህ ግን የገጠመኝ የከፋ ነገር ነው ብላለች።

አር ኤ ኤስ በመባል የሚታወቀው የሀገሪቱ የስደተኞች ሴክሬታሪያት እንዲሁም የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኮሚሽን ሰራተኞች ከ145 እስከ 290 ዶላር የስደተኛ ጥያቄን ለማቀላጠፍ ጉቦ እንደሚጠይቁ ጋዜጣው አጋልጧል።

በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን የፖለቲካና የኢኮኖሚ ስደተኞች ኬንያን እንደመሸጋገሪያና ለጊዜው ሕይወታቸውን ማቆያ እንደሚጠቀሙበት ነገር ግን የሕወሃት የደህንነት ሃይሎች ከኬንያ የጸጥታ ሃይሎች ጋር በመተባበር የፖለቲካ ስደተኞችን በማፈንና ወደ ኢትዮጵያ በመውሰድ ሰቆቃ እንደሚፈጽሙ ሲዘገብ መቆየቱ አይዘነጋም።