በኬንያ አንድ ከፍተኛ የምርጫ ኮሚሽን ባለስልጣን ተገደሉ

(ኢሳት ዜና–ሐምሌ 24/2009) በኬንያ አንድ ከፍተኛ የምርጫ ኮሚሽን ባለስልጣን መገደላቸው ተነገረ።
አንድ ሳምንት በቀረው የኬንያ ምርጫ ባለስልጣኑ መገደላቸው በሀገሪቱ ከፍተኛ ወጥረትን ፈጥሯል
በኬንያ ተገደሉ የተባሉት ባለስልጣን የመረጃና የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር የነበሩና ከፍተኛ የሚባል ሰቆቃ ተፈጽሞባቸው መገደላቸው ተነግሯል።
ቸሪስ ማሳንዶ የተባሉት እኒሁ ባለስልጣን ተገድለው ከመገኘታቸው በፊት ለ3 ቀናት ተሰውረው እንደነበር ሮይተርስ ዘግቧል።
በኬንያ በሚቀጥለው ማክሰኞ አጠቃላይ ሀገራዊ ምርጫ ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል።በዚሁም የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታና ተቃዋሚያቸው ራይላ ኦዲንጋ ከፍተኛ የምርጫ ቅስቀሳ ላይ መሆናቸው ይታወቃል
የባለስልጣሉ መገደል በኬንያ የብሔር ግጭት እንዳይፈጠርና ከምርጫው ጋር የተያያዘ ደም መፋሰስ እንዳይከሰት ተሰግቷል።
የምርጫ ባለስልጣኑ ማን እንደገደላቸውና ለምን እንደተገደሉ የታወቀ ነገር የለም።ከዚሁ ጋር ተያይዞም የምርጫ ቦርድ ባለስልጣናት መንግስት የጸጥታ ጥበቃ እንዲያደርግላቸው ጥሪ አቅርበዋል።
ከግድያው ጋር በተያያዘ ከሀገሪቱ መንግስትና ከጸጥታ ባለስልጣናት የተሰጠ መግለጫ የለም።
በኬንያ በዋነኛ ተቃዋሚነት የሚታወቁት ራይላ ኦዲንጋ ሁለት ጊዜ ለፕሬዝዳንትነት ተወዳድረው ቢሸነፉም ምርጫው የተጭበረበር ነው በማለት ፍርድ ቤት እስከመሄድ ደርሰው ነበር።
ፍርድ ቤቱ ግን ክሳቸውን ውድቅ አድርጎባቸዋል።
በተለይ ደግሞ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2007 ሲሸነፉ ውጤቱን በመቃወም የአደባባይ ሰልፍ በመጥራታቸው በተፈጠረ ብጥብጥ 1 ሺ 200 ኬንያውያን መገደላቸው ይታወሳል።
በአሁኑ የኬንያ ምርጫ የፓርላማ አባላትና የአካባቢ ተወካዮች የሚፎካከሩ ሲሆን ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ለ2ኛ ዙር የሀገሪቱ ርእሰ ብሄር ለመሆን ይወዳደራሉ።
ፕሬዝዳንት ኬንያታ የአሁኑን ምርጫ ካሸነፉ በሀገሪቱ ህገ መንግስት መሰረት የመጨረሻ ጊዜያቸው ይሆናል።