በኦሮሞና በኢትዮጵያ ሶማሌ ተወላጆች መካከል የማፈናቀሉ ሒደት መቀጠሉ ተዘገበ

(ኢሳት ዜና–መስከረም 23/2010) በምስራቅ ኢትዮጵያ በኦሮሞና በኢትዮጵያ ሶማሌ ተወላጆች መካከል የማፈናቀሉ ሒደት መቀጠሉ ተዘገበ።

አካባቢውን በማረጋጋትና መፈናቀሉን በመግታት በኩል ጉልህ ሚና ይኖረዋል ተብሎ የሚጠበቀው የመከላከያ ሰራዊት ተፈናቃዮችን እያጀበ በማመላለስ ላይ መሆኑን በስፍራው ተገኝተው ሂደቱን የተከታተሉ የሀገር ቤት ጋዜጦች ዘግበዋል።
እስካለፈው ሳምንት ብቻ የኦሮሞ ተፈናቃዮች ቁጥር 67 ሺ መድረሱም ተመልክቷል።

በኦሮሚያ ክልልና በኢትዮጵያ ሶማሌ አዋሳኝ አካባቢ የተፈጠረውን ግጭት ተከትሎ የነዋሪዎቹ መፈናቀል እስከባለፈው ሳምንት መቀጠሉን በሀማሬሳ መጠለያ ጣቢያ ተገኝቶ ሪፖርቱን ያጠናቀረው የሪፖርተር ጋዜጣ ዘጋቢ እንዳመለከተው ከሶማሌ ክልል የተፈናቀሉት የኦሮሞ ተወላጆች ቁጥር 67 ሺ ደርሷል።

ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ የሶማሌ ተወላጆችም መፈናቀላቸው ታውቋል።

የማፈናቀሉ ሂደት በመቀጠሉም በመከላከያ ሰራዊት አባላት እየታጀቡ ወደ ሶማሌ ክልል በመሔድ ላይ ይገኛሉ።

የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ለማ መገርሳና የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ አብዲ መሀመድ የሰላም ስምምነት ለሁለተኛ ጊዜ መፈራረማቸውም ይሁን የመከላከያ ሰራዊት መግባት ግጭቱን ከማቆም ባሻገር መፈናቀሉን መግታት ብሎም ሰላም ማምጣት አልቻለም።

ጳጉሜ 3/2009 የጀመረውና በተለይም በአዲሱ አመት መጀመሪያ መስከረም 1፣2 እና 3 ተጠናክሮ በቀጠለው ማፈናቀል በርካቶች ቀያቸውን ጥለው ተሰደዋል።

ከጅጅጋ ከተባረሩት የኦሮሞ ተወላጆች አንዱ የሆነውና የአራት ልጆች አባት የ32 አመቱ ራይስ አባሜጫ ከልጅነቱ ጀምሮ በኖረባትና አድጎ የሆቴል ባለንብረት ከሆነባት ጅጅጋ በመባረሩ መድረሻ ማጣቱን ገልጿል።

ከጅጅጋ ውጭ የማውቀው የለም ያለው ራይስ አባሜጫ አሁን ላይ ወደ ማያውቀው ቦታ መባረሩን ይናገራል።

ኦሮሞዎችን የሚያባርሩት ሰዎች ምሽት በየቤቱ እየዞሩና የኦሮሞ ተወላጆችን እያሰሱ ድርጊቱን እንደፈጸሙም ገልጿል።
ከሴቶቹ ይልቅ ደግሞ የኦሮሞ ወንዶች ላይ የጭካኔ ድርጊት እንደሚፈጸምባቸም ተናግሯል።

ራይስ አባሜጫ እንደሚለው በሆቴሉ አካባቢ የነበረ ቀማኛ ቡድንም ገንዘብና ንብረቱን ባለቤቱን በማስፈራራት ወስዶበታል።

በሶማሌ ክልል በኦሮሞ ተወላጆች ላይ እስርና እንግልቱ የሚፈጸመው ደግሞ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ባሉበት እንደሆነም ከዘገባው ለመረዳት ተችሏል።

ደገሀቡር ላይ ታፍሰው ወደ እስር ቤት ከተወሰዱ የኦሮሞ ተወላጆች አንዱ የሆነው ስለሺ ሞቲ መስከረም 3/2010 ከእስር ቤት መውጣት የቻለው በግል በሚያውቀው የ50 አለቃ ማዕረግ ባለው የመከላከያ ሰራዊት አባል መሆኑን ገልጿል።
ይህም ድርጊቱ የሚፈጸመው የመከላከያ ሰራዊቱ ባለበት መሆኑን የሚያረጋግጥ ሆኗል።

በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል አዋሳኝ የተፈጠረው ግጭት በሕዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ አቀነባባሪነት በሁለቱ ወንድማማች ሕዝብ መካከል እንደተፈጸመ የፖለቲካ ተንታኞች ሲገልጹ መቆየታቸው ይታወሳል።

በተያያዘ ዜና ከኦሮሚያ ክልል ባሌ ዞን የተፈናቀሉትና ቁጥራቸው ከ2 ሺ በላይ የሆኑት የሲዳማ ተወላጆች ወደ ነበሩበት መመለሳቸው ታውቋል።

በሀገር ሽማግሌዎች በተመራ የእርቅ ሒደት የሲዳማ ተወላጆቹ ወደ ነበሩበት ባሌ ዞን ተመልሰው ሰላማዊ ሕይወታቸውን መቀጠላቸው ተመልክቷል።