በኦሮሚያ ክልል ይፋ ከተደረገው የኢኮኖሚ አብዮት ጋር ተያይዞ ችግር መፈጠሩ ተገለጸ

ሰኔ 21 ፥ 2009

በኦሮሚያ በቅርቡ ይፋ ከተደረገው የኢኮኖሚ አብዮት ጋር ተያይዞ ከፍተኛ ምስቅልቅል እየተፈጠረ መሆኑ ተገለጸ። በክልሉ በባለሃብቶች ተይዘው የነበሩ ስራዎች ለወጣቶች እንዲሰጡ ጫና እየተደረገ በመሆኑ በኢንቨስትመንት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ ይገኛል።

በኦሮምያ የኢኮኖሚ አብዮት በሚል እየተቀነቀነ ያለው ባለፈው ጊዜ በክልሉ የነበረውን ተቃውሞ ለማብረድና ወጣቶችን ስራ ለማስያዝ በሚል እንደሆነ ይነገራል ። የኢኮኖሚ አብዮቱ በርካታ በአክሲዮን የሚመሩ ኢንዱስትሪዎች እንደሚገነቡ እቅድ እንዳለው ቢነገርም ለእቅዱ የሚያስፈልገው በጀት ግን ከህዝቡ እንዲሰበሰብና ባለሃብቶች እንዲያሟሉ የሚጠበቅ ነው። በአክሲዮን ማህበራቱ የክልል መንግስት ድርሻ ይኖረኛል ቢልም በተጨባጭ የታየ ነገር አለመኖሩ ነው እየተነገረ ይገኛል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በኦሮምያ ከታቀደው የኢኮኖሚ አብዮት ጋር ተያይዞ ከፍተኛ ምስቅልቅል እየተፈጠረ መሆኑን መረጃዎች አለመከቱ። በክልሉ ያሉ ባለሃብቶች ስራቸውን እየተዉ ለወጣቶች ይስጡ መባሉ በርካታ ኢንቨስተሮችን እያበሳጨ ይገኛል ተብሏል። ከትንሽ እስከ ትልቅ ያሉ ኢንቨስተሮችን በጅማ ከተማ ብቻ በ5 ባለሃብቶች ተይዞ የቆየ ከ10 ሄክታር በላይ ካባ የድንጋይ ማምረቻ መሬት ለ380 የአካባቢው ወጣቶች እንዲሰጥ ተደርጓል ። በከተማዋ ኢፋ ቡላ ቀበሌ የሚገኘው የድንጋይ ካባ ከባለሃብቶች የተነጠቀው በህገወጥ መንገድ መሆኑን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ሰዎች ገልጸዋል።

በቅርቡ በኦሮሚያ ግዙፍ ሲሚንቶ ፋብሪካ የገነቡት ናይጄሪያዊው ባለሃብት አሚልተን ዳንጎቴ የአሸዋ የሸክላና የፑሚስ ስራውን ጥለው ለመውጣት መዛታቸው ይታወሳል ። ባለሃብቱን ለማግባባትና ሁኔታውን ለመመርመር የተወካዮች ምክር ቤት የንግድና የኢንዱስትሪ  ቋሚ ኮሚቴ ወደ ስፍራው ማቅናቱም ተነግሯል። በክልሉ የለገደምቢ ወርቅን በማውጣት ላይ ያሉት ሼህ መሃመድ አላሙዲን የስራ ፈቃዳቸውን ለማደስ መጠየቃቸውን ተከትሎ የኦሮምያ መንግስት ጣልቃ እየገባ መሆኑም እየተነገረ ነው።