በኦሮሚያ ክልል የተጀመረው ተቃውሞ እንደቀጠለ ነው

(ኢሳት ዜና–ጥቅምት 9/2010) በኦሮሚያ ክልል የተጀመረው ተቃውሞ ተባብሶ ቀጥሏል።

ትላንት ምሽት የተጀመረው የገብረጉራቻው አመጽ በርካታ የመንግስት ተሽከርካሪዎችን በእሳት በማቃጠል ተካሂዷል።

ዛሬ በአምቦና በወለጋ ሆሮጉድሩ ሕዝብ አደባባይ በመውጣት የህወሃት መንግስት ከስልጣን እንዲወርድ ጠይቋል።

ሕዝባዊ ተቃውሞው በተለያዩ አካባቢዎች በመደረግ ላይ ነው።

ከ20 በላይ ተሽከርካሪዎች ተቃጥለው። በርካታ ቤቶች በእሳት ወድመዋል። ህዝቡ ይህን እርምጃ ሲወስድ በተጠናና በስልጣን ላይ ካለው ስርዓት ጋር ግንኙነት ካላቸው ጋር የተያያዘውንና የመንግስት ታርጋ ያላቸውን እየለየ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።

ገብረጉራቻ ከትላንት ጀምሮ በህዝባዊ አመጽ ውስጥ ናት። ሙከጡሪ፣ ፍቼን ይዞ ያለው መስመር ጠንካራ የህዝብ ተቃውሞ በመካሄድ ላይ ነው።

ትላንት ገብረጉራቻ ላይ የተቃጠሉት በርካታ ተሽከርካሪዎች የህዝብ ምሬት የደረሰበትን ደረጃ ያሳያል የሚለው አስተያየት ከየአቅጣጫው እየተሰማ ነው። ሰላማዊው ህዝብ እንዳይጎዳ ከፍተኛ ጥንቃቄ ተደርጓል የሚሉ በአካባቢው የነበሩ የዓይን እማኞች በስልጣን ላይ ላለው ስርዓት ግልጽ መልዕክት የተላለፈበት እንደሆነም ገልጸዋል።

ዛሬም በአካባቢው ያለው የህዝብ ተቃውሞ እንደቀጠለ ሲሆን ብዛት ያለው የአጋዚ ሰራዊት እንዲገባ መደረጉን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

በሌላ በኩል የአምቦ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች የህወሀት አገዛዝ እንዲያከትም በመጠየቅ በግቢያቸውና በአምቦ ከተማ ዋና ዋና መንገዶች ላይ ተቃውሞ ማድረጋቸው ታውቋል።

በአምቦ ዩኒቨርስቲ ቅጥር ግቢ ታስቦ የተጀመረውን ተቃውሞ የከተማው ህዝብ በመቀላቀሉ ወደ አደባባይ ሊወጣ መቻሉን ከስፍራው የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

በወለጋ ሆሩ ጉድሩም በተመሳሳይ ህዝባዊ ተቃውሞ መካሄዱን የገለጹት የኢሳት ምንጮች የህወሃት መንግስት እንዲወርድና ስልጣኑን ለህዝብ እንዲያስረክብ ጠይቀዋል።

በሌላ በኩል በሰሜን ሸዋ በገብረጉራቻ ሙከጡሪና ፍቼ እየተካሄደ ያለው ተቃውሞ ኩታ ገጠም በሆኑ የአማራ ክልል ከተሞችና መንደሮች ትኩሳት በመፍጠር ላይ መሆኑን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

በሙከጡሪ ከተማ ተገንጥለው ያሉት ቆላማዎቹ ለሚ እና መርሃቤቴ ከተሞች ፣ በጎጃም ደጀን ሉማሜ ከተሞች ህዝባዊ አመፁ ዳር ዳር እያለባቸው እንደሆነ እየተነገረ ነው።

ከአዲስ አበባ ዳርቻ ከሱሉልታ እስከ ጉሃፅዩን ድረስ የተዛመተው ህዝባዊ ተቃውሞ ወደ ጎጃምና ሰሜን ሸዋ እንዳይዛመት በመስጋት የህወሀት አገዛዝ ሰራዊቱን በብዛት ማስፈሩን የአይን እማኞች ገልጸዋል።

ከኦሮሚያ ክልል ወደ አማራው የሚወስዱ መስመሮች በተቃውሞ ምክንያት በመዘጋታቸው የትራንስፖርት አገልግሎት በአብዛኛው መቋረጡም ታውቋል።