በኦሮሚያ ክልል የቡራዮ ከተማን ሁለት ከንቲባዎች ጨምሮ 25 የአካባቢው ባለሥልጣናት ታሠሩ

ሚያዚያ ፰ (ስምንት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ፍኖተ ነፃነት ምንጮቹን ጠቅሶ እንደዘገበው የከተማው ከንቲባ አቶ ቸርነት ጉርሜሳና የቀድሞ የከተማው ከንቲባ አቶ ኃይሉ ደቻሳ ከሌሎች 23 የአካባቢው ባለሥልጣናት ጋር በሙስና ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር ውለዋል፡፡

“ቡራዮ”በየደረጃው ያሉ የመንግስት ባለሥልጣናት “በካሽ ልምጣ ወይስ በክላሽ?” እያሉ መሬት የዘረፉበት አካባቢ ነው እየተባለ በቀልድ መልክ  በስፋት ይወራል።

የታሠሩት የአካባቢው ባለስልጣናት  እርስ በርስ በጥቅም በመቆላለፍ በተለያየ ሰው ስም በተደጋጋሚ መሬት በመውሰድና በመሸጥ ከፍተኛ ሙስና መፈፀማቸው ተገልጿል።

ከኢትዮጵያ ያለፉትን ሦስት ዓመታት ሳይጨምር በህገ-ወጥ መንገድ ወደ ውጪ የወጣው ገንዘብ ከ 12 ቢሊዮን ዶላር በላይ እንደሆነ ዓለማቀፍ ድርጅቶች ይፋ ያደረጉት ሪፖርት ያመለክታል።

ይሀ ሀቅ ይፋ ቢሆንም፤ ከተቋቋመ  ከአስር ዓመታት በላይ ያስቆጠረው የፀረ-ሙስና ኮሚሽን  አንድንም ከፍተኛ የመንግስት ባለሥልጣናት በሙስና ለመክሰስና ለማስቀጣት አለመድፈሩ ብዙዎችን አስገርሟል።

ኮሚሽኑ የአስር ዓመት ጉዞውን በቅርቡ  ሲያከብር  ጥናት ያቀረቡ አንድ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሁር፦ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ባለፉት አስር ዓመታት ከ 500 በላይ ሰዎችን በሙስና እንዳስቀጣ ካመለከቱ በሁዋላ፦”ሆኖም ከነዚህ ሰዎች መካከል አንድም ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣን የለም።በመንግስት ስልጣን ላይ ከተቀመጡት ውስጥ በሙስና የተከሰሱት አነስተኛ ስልጣን ያላቸው ናቸው። ኮሚሽኑ ከፍተኛ የመንግስት ተሿሚዎችን ይፈራል”ማለታቸው አይዘነጋም።

________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide