በኦሮሚያ ክልል በወለጋ፣ በኢሉባቦርና በጂማ ሊሙ ገነት ተቃውሞ ተካሄደ

(ኢሳት ዜና–ጥቅምት 10/2010) በኦሮሚያ ክልል በወለጋ፣ በኢሉባቦርና በጂማ ሊሙ ገነት ተቃውሞ መካሄዱ ተገለጸ።

በሊሙ ገነት ህዝቡ ሰፋፊ የቡና ማሳዎችን በመቆጣጠር እየተከፋፈለው መሆኑንም ከስፍራው የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

ተቃውሞው ኩታ ገጠም በሆኑ የአማራ ክልል መንደሮችም መግባቱ እየተነገረ ነው።

በኢሉባቦር በተካሄደው ተቃውሞ ሁለት ሰዎች ተገድለዋል።

በሰሜን ሸዋ ደራ ጉንዶ መስቀል ከተማ በነበረው ተቃውሞ በመንግስት ታጣቂዎች በተወሰደ እርምጃ 2 ሰዎች መገደላቸውንና 8 ሰዎች መቁሰላቸውን የኢሳት ምንጮች ካደረሱን መረጃ ለማወቅ ተችሏል።

በቡና ምርቷ የምትታወቅ ናት። በጂማ ዞን ውስጥ የምትገኘዋ አነስተኛ ከተማ – ሊሙ ገነት።

ሰፋፊ የእርሻ ልማቶች በሚከናወኑባት ሊሙ ገነት ህዝባዊ ተቃውሞ ሲካሄድባት የመጀሪያዋ አይደለም።

ሰሞኑን እየተካሄደባት ያለው ግን በምሬት የታጀበና በህዝብ ቁጣ የደመቀ እንደሆነ ይነገራል።

ከትላንት በስቲያ የተጀመረውና በከተማዋ ዙሪያ ያሉትን መንደሮች ባካተተው ተቃውሞ ህዝቡ የቡና እርሻዎችን በመቆጣጠር እየተከፋፈለው መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች ለኢሳት ገልጸዋል።

ፌደራል ፖሊስ ከአቅሙ በላይ በመሆኑ የእርሻ ማሳዎቹን መጠበቅ እንዳልቻለ ታውቋል። ህዝቡ መንግስት የለም እያለ እንደሆነም ያነጋገርናቸው ገልጸዋል።

ዛሬ በተካሄዱት የተቃውሞ ሰልፎች በትንሹ አራት ሰዎች መገደላቸው ተገልጿል።

ከ10 በላይ የሚሆኑት በመንግስት ታጣቂዎች በተፈጸመባቸው ጥቃት መቁሰላቸው ታውቋል።

ግድያዎቹ የተፈጸሙት በኢሉባቡር በደሌ ከተማና በሰሜን ሸዋ ዞን ጉንዶ መስቀል መሆኑም ተመልክቷል።

በኢሉባቡር ጮራ ከተማ ትላንት የጀመረው ተቃውሞ ዛሬም የቀጠለ ሲሆን የመንግስት ከፍተኛ ባልስልጣናትን በተለይም የህወሀት ሹማምንቶችን በስም እየጠሩ ወንጀለኛ እንደሆኑ ሲገለጽ እንደነበርም ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በበደሌ ከተማ ስሶተኛ ቀኑን ባስቆጠረው ተቃውሞም ህዝብ የህወሀት መንግስት ከስልጣን እንዲወርድ መጠየቁንም የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል።

ተካ በንቲና ገመቹ ኦላና የተባሉ ሁለት ወጣቶች መገደላቸውም ታውቋል።

በሰሜን ሸዋ ዞን ደራ ወረዳ ጉንዶመስቀል ከተማ ከትናንት ጀምሮ የተነሳው ተቃውሞ ዛሬም ቀጥሎ ውሏል።

የስርዓት ለውጥ እንጠይቃለን የሚሉ ድምጾች በብዛት መሰማታቸውን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ሁሉም ብሄሮች በአንድነት ተሰልፈው ወደ አደባባይ በመውጣት ተቃውሞ ያሰሙ ሲሆን የፌደራል አድማ በታኝ አካባቢውን ቢቆጣጠርም ከህዝቡ ጋር ተፋጦ ይገኛል።

እስካሁን 2 ሰዎች መገደላቸውንና 8 ሰዎች መቁሰላቸውን ማረጋገጥ ተችሏል።

በወለጋ ሆሮ ጉድሩም ትላንት የተጀመረው ተቃውሞ የቀጠለ ሲሆን ህዝቡ በነቂስ በመውጣት የህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ መንግስት ከስልጣን እንዲወርድ መጠየቁን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።