በኦሮሚያ ክልል በሺዎች የሚቆጠሩ ሚሊሺያዎች ስልጠና እየወሰዱ ነው

ግንቦት ፴ ( ሠላሳ ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በቅርቡ በሶማሊያና በኦሮሚያ ድንበሮች አካባቢ የተነሳውን ግጭት ተከትሎ የኦሮምያ ክልል በርካታ ልዩ ሚሊሺያዎችን ማሰልጠን መጀመሩን ምንጮች ገልጸዋል። የሚሊሺዎቹ ስልጠና በሶማሌ ክልል ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ነው ሲሉ የሶማሊ ክልል ፕሬዚዳንት አቤቱታ አቅርበዋል።
የኢሳት ምንጮች እንደገለጹት ከእያንዳንዱ የኦሮሚያ ወረዳ 8 አጠቃላይ ከ362 የኦሮሚያ ወረዳዎች 2896 የሚሆኑ እድሜያቸው ከ18 እስከ 30 የሚሆኑ ወጣቶች ተመልምለው በአዳማ ፖሊስ ማሰልጠኛ ጣቢያ ወታደራዊ ነክ ስልጠናዎችን እየወሰዱ ነው። ዋናው ስልጠናም አነጣጥሮ መተኮስ ላይ ያተኮረ ነው።
በእንጭኔም ተመሳሳይ ቁጥር ያላቸው ወጣቶች ለስልጠና የገቡ ሲሆን፣ የፊታችን ነሃሴ ይመረቃሉ ተብሏል። እነዚህ ተመርቀው ሲወጡ ደግሞ የኦሮምያ ልዩ ሃይል እና የኦሮምያ ፖሊስ ለተሃድሶ ስልጠና ወደ ማሰልጠኛ ይገባሉ።
የኦሮምያ አስተዳደር ወጣቶችን እየመለመለ ማሰልጠኑ ለሶማሊ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ አብዲ ሙሃመድ ኡመር የሚዋጥላቸው አልሆነም። አቶ አብዲ የኦሮምያ ክልል ልዬ ሚሊሺያዎችን የሚያሰለጥነው በሶማሊ ክልል ላይ ጥቃት ለመፈጸም ነው ሲሉ በቅርቡ ጄ/ል ሳሞራ የኑስ በሰበሰቡት መድረክ ላይ ተናግረዋል። የአቶ አብዲ አቤቱታ ግን በጄ/ል ሳሞራ በኩል ትኩረት ሳያገኝ ቀርቷል።
ነገሮች በግልጽ ባልተገለጹበት ሁኔታ አቶ አብዲ ሰሞኑን በምስራቅ ኦሮምያ፣ ባቢሌ፣ ጉርሱምና በጭናክሰን ህዝቡን ሰብስበው ይቅርታ የጠየቁ ሲሆን፣ ህዝቡም ይቅርታ መጠየቅ ብቻ ሳይሆን፣ ከዚህ በሁዋላ ጥቃት እንደማይፈጸመብን ዋስትና ያስፈልገናል፣ እንዲሁም ለሞቱት ወገኖቻችንና ለወደመብን ንብረት ተገቢው ካሳ ሊከፈለን ይገባል የሚል ጥያቄ አቅርቧል። አቶ አብዲ ከእንግዲህ በእኔ ትእዛዝ ጥቃት ቢፈጸም ለህግ አቅርቡኝ ያሉ ሲሆን፣ የካሳውን ጉዳይ ግን ምላሽ ሳይሰጡበት አልፈውታል።