በኦሮሚያ ክልል ሶዳ ከተማ ዛሬ የመከላከያ ሰራዊት በወሰደው ርምጃ ስድስት ሰዎች ተገደሉ

(ኢሳት ዜና–ጥቅምት 2/2010) በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን ድሬ ወረዳ ሶዳ ከተማ ዛሬ የመከላከያ ሰራዊት በወሰደው ርምጃ ስድስት ሰዎች ተገደሉ።

ከ20 በላይ ሰዎች መቁሰላቸውም ታውቋል።

መሳሪያ ጭነው ወደሶማሌ ክልል እያጓጓዙ ነው ተብለው በነዋሪው መንገድ የተዘጋባቸው ስምንት የመከላከያ ተሽከርካሪዎች ላይ የነበሩ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ህዝቡ ላይ ተኩስ መክፈታቸውንም ከአካባቢው የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

ማምሻውን በሶዳ ሜጋ ያቤሎ፣ ዱብሉቅና ሞያሌ መንገዶች መዘጋታቸው የተገለጸ ሲሆን መሳሪያ ጭነዋል የተባሉት የመከላከያ ተሽከርካሪዎችም ከሶዳ ከተማ እስከምሽት ድረስ መውጣት እንዳልቻሉ ታውቋል።

በሶማሌና ኦሮሚያ ክልሎች የተነሳው ግጭት ከተከሰተባቸው አከባቢዎች አንዱ በሆነው የቦረና ዞን ዳግም ውጥረት እንዲነግስ ያደረገው የዛሬው ግድያ መነሻው መሳሪያ ጭነዋል የተባሉት የመከላከያ ተሽከርካሪዎች ናቸው።

መነሻቸው ከመሃል ሀገር እንደሆነ የሚገመተውና በፒክ አፕ መኪና ፊት መሪነት ወደሶማሌ ክልል አቅጣጫ እየገሰገሱ የነበሩት ስምንት የመከላከያ ከባድ ተሽከርካሪዎች ዲሬ ወረዳ ሶዳ ከተማ ሲደርሱ በህዝብ ተቃውሞ ጉዟቸውን መቀጠል አልቻሉም።

ነዋሪዎች እንደሚሉት የጫኑት መሳሪያ በመሆኑ ህዝቡ ሊያሳልፋቸው አልፈቀደም። መንገድ ዘግቶ አቆማቸው።

እዚያው በግጭቱ ስፍራ ከተገደሉት በተጨማሪ ሆስፒታል ከተወሰዱት አንድ ሰው ተጨምሮ በድምሩ ስድስት ሰዎች በመከላከያ ሰራዊት ተኩስ መገደላቸውን ነው ለማወቅ የተቻለው።

ነዋሪው እንደሚለው ተሽከርካሪዎቹ የጫኑት የጦር መሳሪያ ነው። ይዘው የሚጓዙት ደግሞ ለሶማሌ ክልል ልዩ ሃይል ነው።

የምንገደልበት መሳሪያ በአጠገባችን ሲያልፍ ዝም ብለን ማየት አንችልም ያሉት የሶዳ ከተማ ነዋሪዎች ከያሉበት ተጠራርተው መንገድ በመዝጋት ያቆሟቸው ሲሆን ከግድያውም በኋላ መሳሪያ የጫኑት ተሽከርካሪዎች እስከምሽት ድረስ ማለፍ እንዳልቻሉ መረጃዎች ያመለክታሉ። አሁንም መከላከያና ህዝቡ ተፋጦ እንዳለ ይነገራል።

መከላከያ ሰራዊት በወሰደው እርምጃ ከ20 በላይ ሰዎች ቆስለዋል።

የኦሮሚያ ፖሊስ ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር በመሆን ድርድር የተጀመረ ሲሆን በአብዛኛው የቦረና ዞን አካባቢ የህዝብ ቁጣ ቀስቅሷል።

ዱብሉቅ፣ ሞያሌ፣ ያቤሎ፣ ሜጋና በሌሎች አከባቢዎችም መንገዶች የተዘጉ ሲሆን መሳሪያ ጭነዋል የተባሉት ተሽከርካሪዎች እንዳያልፉ በየቦታው መንገዶች በድንጋይና በትላልቅ ዛፎች መዘጋታቸውንም የደረሰን መረጃ ያመለክታል።