በኦሮሚያ በዴሳ ከተማ ሁለት ሰዎች በመንግስት ጸጥታ ሃይሎች ተገደሉ

ኢሳት (ሃምሌ 26 ፥ 2008)

በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ሃረርጌ ዞን ስር በምትገኘው የበዴሳ ከተማ ማክሰኞ ተጨማሪ ሁለት ሰዎች በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች ተገደሉ። bedessa

በከተማዋ ሰኞ የተገደሉት ሁለት ሰዎችን ማክሰኞ ለመቅበር በተካሄደ ስነ-ስርዓት ላይ የጸጥታ ሃይሎች ተኩስ በመክፈት ተጨማሪ ሁለት ሰዎች እንዲሞቱ ማድረጋቸውን እማኞች ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ አስረድተዋል።

የአራቱ ሟቾችን ስም በመጥቀስ ስለድርጊቱ እማኝነታቸውን የሰጡት የበዴሳ ከተማ ነዋሪዎች በከተማዋ ከፍተኛ የጸጥታ ስጋት መኖሩን አክለው አስረድተዋል።

ሰኞ በከተማዋ የተካሄደውን ተቃውሞ ተከትሎ የመንግስት መስሪያ ቤቶች አገልግሎት መስጠት ያቆሙ ሲሆን ቁጥራቸው በትክክል ያልታወቁ ነዋሪዎችን ለእስር መዳረጋቸው ታውቋል።

በከተማዋ ቁጥሩ ከፍተኛ የሆነ የጸጥታ ሃይል ተሰማርቶ የሚገኝ ሲሆን፣ ከ20 የሚበልጡ ሰዎች ከፍተኛ ድብደባ ተፈጽሞባቸው ለህክምና ሆስፒታል መግባታቸውን ለደህንነታቸው ሲሉ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ እማኞች ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ አስታውቀዋል።

በበዴሳ ከተማ አጎራባች የሚገኙ የገጠር ከተማ ነዋሪዎች ወደ በዴሳ ከተማ በመጓዝ ህዝባዊ ተቃውሞውን መቀላቀላቸው ታውቋል።

የጸጥታ ሃይሎች ከተለያዩ አካባቢዎች ወደ ከተማዋ የሚገቡ ሰዎችን ለመግታት የሃይል እርምጃ እንደሚወስዱ የተናገሩት ነዋሪዎች ከተማዋ በአሁኑ ወቅት ምንም አይነት እንቅስቃሴ እየተካሄደባት እንዳልሆነ ለመረዳት ተችሏል።

በአካባቢው ዳግም እየተካሄደ ባለው በዚሁ ህዝባዊ ተቃውሞ ነዋሪዎች ለእስር የተዳረጉ ሰዎች እንዲፈቱና በክልሉ የሰብዓዊ መብት እንዲከበር በመጠየቅ ላይ መሆናቸውን እማኞች ለኢሳት ገልጸዋል።