በእስር ቤት ለወራት ታስረው የሚገኙ የነጻነት ታጋዮች ለችግር ታድርገዋል

ሚያዝያ ፲፩ (አሥራ አንድ ) ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉና የእስረኞችን ሁኔታ የሚከታተሉ ሰዎች ለኢሳት እንደገለጹት ለመብታቸው በተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች ውስጥ ገብተው ሲታገሉ የነበሩ፣ በግላቸው በአገሪቱ የሚታዩ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ሲያጋልጡ እንዲሁም በጋዜጠኝነት ሙያ ተሰማርተው ለአገራቸው የሚችሉትን መስዋትነት በመክፈል ላይ ያሉ ኢትዮጵያውያን በእስር ቤት ውስጥ ከሚደርስባቸው ስቃይ በተጨማሪ፣ መሰረታዊ የሚባሉትን ልብስ እና ጫማዎችን ለመቀየር አልቻሉም።
ከአማራ እና ኦሮምያ አካባቢ የመጡ እስረኞች በተለዬ ለከፍተኛ ስቃይ መደረጋቸውን የሚገልጹት ታዛቢዎች፣ ድርጊቱ የዘር ማጥፋት ተብሎ ሊፈረጅ የሚችል ነው ይላሉ። ከሰሜን ጎንደር የመጡ እስረኞች አብዛኞቹ እየታመሙ እየወደቁ ነው የሚሉት ታዛቢዎች፣ አቶ አንጋው ተገኝ በደረሰበት ድብደባ መስማት እንደተሳነው ፣ አባይ ዘውዱም በልብና በጉበት በሽታ እየተሰቃየ መሆኑን ገልጸዋል።
ቅያሬ ልብስ አጥተው የሚቸገሩ በርካታ እስረኞች እንዳሉ የሚገለጹት እነዚሁ ወገኖች፣ በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያን ሰዎቹን በህይወት እያሉ እንዲደግፉ ጥሪ አቅርበዋል