በኢትዮጵያ ያለው የዋጋ ንረት ተባብሶ ቀጥሏል

ታኅሣሥ ፳፯ (ሃያ ሰባት)ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- የኢትዮጵያ ማእከላዊ ስታስቲክስ ኤጀንሲ ባወጣው ወርሃዊ የዋጋ ጥናት ሪፖርት መሰረት በታህሳስ ወር የታየው የዋጋ ንረት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር 7.3% ጭማሪ አሳይቷል። በታህሳስ ወር 2009 ዓ.ም የምግብ ነክ የዋጋ ንረት 6.5% ጭማሪ ያሳየ ሲሆን ምግብ ነክ ያልሆኑ ሸቀጦች በበኩላቸው 8.1% ጭማሪ ታይቶባቸዋል። ይህም በአጠቃላይ የአስራ ሁለት ወራት ተንከባላይ የዋጋ ግሽበት ረዘም ላለ ጊዜ መቀጠሉን ኤጀንሲው አስታውቋል።

በአገር አቀፍ የችርቻሮ ዋጋ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር 6.7% በመቶ ጭማሪ አሳይቷል። የምግብ እና አልኮል ያልሆኑ መጠጦች 5.3%በመቶ፣ ልብስና መጫሚያ 2.7%በመቶ፣ የቤት ኪራይ፣ የቤት  መስሪያ እቃዎች፣ ውሃ እና ኢነርጂ 14.5%በመቶ እና ሌሎችም ጭማሪ በማሳየታቸው ምክንያት የዋጋ ንረቱ ተከስቷል።

ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በመላው ኢትዮጵያ የምግብ ዋጋ ንረት በከፍተኛ ሁኔታ ጫማሪ ታይቶበታል። ዳቦና እህል 5.6%በመቶ፣ ሥጋ8.9%በመቶ፣ ወተት አይብና እንቁላል 8.8%በመቶ፣ ዘይትና ቅባቶች 2.5%በመቶ፣ ፍራፍሬ 5.2%በመቶ፣ አትክልት፣ ጥራጥሬ፣ ድንችና ሌሎች ስራስሮች 4.7%በመቶ፣ ስኳር ማርና ቼኮሌት 28.8%በመቶ፣ አልኮል ያልሆኑ መጠጦችና ቡና 20.2%በመቶ የዋጋ ጭማሪ መከሰቱን የኢትዮጵያ ማእከላዊ ስታስቲክስ ኤጀንሲ ዝርዝር ጥናታዊ ሪፖርት ያሳያል።

የምግብ ዋጋ ጭማሪ የታየባቸው የአገሪቱ ክልሎች ውስጥ በደቡብ ክልል 13.2 በመቶ  ከፍተኛው የዋጋ ጭማሪ የተከሰተ ሲሆን ፣ በሶማሌ ክልል 9.8 ፣ በአማራ ክልል 8.5 ፣ በድሬደዋ መስተዳድር 7.7 ጭማሪ ታይቷል።

በአፋር 0.1 በመቶ እና በኦሮሚያ 1.4% በመቶ የዋጋ ቅናሽ ታይቶባቸዋል።