በኢትዮጵያ ያለው የህዝብ በደልና የፍትህ እጦት በሽምግልና የሚፈታ አይደልም ተባለ        

(ኢሳት ዜና –ሐምሌ 13/2009)በመቀሌ ከተማ ከሐምሌ 14 እስከ 16/2009 ይካሄዳል የተባለው የአማራና የትግራይ ሽማግሌዎች ስብሰባ አላማው በግልጽ አልተቀመጠም።

ይህም ሆኖ ግን ከአማራና ከትግራይ ክልል የተውጣጡ 1 ሺ 200 የሚሆኑ የሀገር ሽማግሌዎች  የክልሎቹ ፕሬዝዳንቶች አቶ ገዱ አንዳርጋቸውና አቶ አባይ ወልዱ በተገኙበት ይካሄዳል ነው የተባለው።

ከአማራ ክልል 4 መቶ የሀገር ሽማግሌዎች ናቸው የተባሉ የብአዴን ካድሬዎችን ጨምሮ መቀሌ ከተማ ገብተዋል።

ታዛቢዎች እንደሚሉት የወልቃይት የማንነት ጥያቄን ተከትሎ ከተነሳው ህዝባዊ ቁጣ ጋር ተያይዞ የአገዛዙ ባለስልጣናት በሁለቱ ክልሎች ህዝቦች መካከል መቃቃርን እየፈጠሩ ናቸው።

ይህንኑ ተለትሎም በስፖርት ሜዳዎችና በዩኒቨርስቲዎች በአማራና ትግራይ ብሄሮች መካከል ግጭቶችና በጥላቻ ላይ የተመሰረቱ ክስተቶች በብዛት በመታየት ላይ ናቸው።

በቅርቡ እንኳን 4 የአማራ ተወላጆችና አንድ የኦሮሞ ተወላጅ በትግራይ ባሉ ዩኒቨርስቲዎች ተገድለው አስከሬናቸው ወደየ ትውልድ ቀያቸው መመለሱ ነው የሚነገረው።

በአማራና ትግራይ የሀገር ሽማግሌዎች ይካሄዳል ስለተባለው ስብሰባ አቶ ነጋሲ በየነና አቶ አይሸሽም ሰለሞን የተባሉ የየአካባቢው ተወላጆች ለኢሳት አስተያየት ሰጥተዋል።

የትግራይ ተወላጅ የሆኑት አቶ ነጋሲ በየነ የችግሩ መንስኤ በህወሃት የሚመራው አገዛዝ ነው ይላሉ።

የአማራ ተወላጁ አቶ አይሸሽም ሰለሞንም በአቶ ነጋሲ በየነ ሃሳብ ይስማማሉ።

ሁለቱም አስተያየት ሰጪዎች በህወሃት/ኢህአዲግ የሚመራው አገዛዝ ህዝብና ህዝብ የተጣላ በማስመሰል የሀገር ሽማግሌዎች ስብሰባ መጥራቱ ቲያትርና ፌዝ ነው ባይ ናቸው አቶ ነጋሲ በየነ።

እንደ አቶ አይሸሽም ሰለሞን ገለጻም ለስብሰባ የተጠሩት የሀገር ሽማግሌዎች እውነተኛ ከሆኑ አገዛዙ የሚፈጽመውን ወንጀል እንዲያቆምና ስልጣኑን እንዲለቅ መጠየቅ ይኖርባቸዋል።

አቶ ነጋሲ በየነም ሆኑ አቶ አይሸሽም ሰለሞን አሁን በኢትዮጵያ ላለው መጠነ ሰፊ የሕዝብ የበደልና ችግር መፍትሄው አድሎአዊ የሆነው ስርአትና አገዛዝ ከስልጣን ሲወርድ ብቻ ነው።

ህወሃትና ብአደኤን የገዢና ተላላኪ ግንኙነት እንጂ ቅራኔ አላቸው ብዬ አላምንም ይላሉ አቶ አይሸሽም።