በኢትዮጵያ ያለው አገዛዝ የኢኮኖሚ እድገት አስመዝግቤያለሁ በሚል በሕዝብ ላይ የሚያደርሰውን በደል ለመሸፋፈን እየሞከረ መሆኑ ተገለጸ

(ኢሳት ዜና–መስከረም 5/2010)በኢትዮጵያ ያለው አገዛዝ የኢኮኖሚ እድገት አስመዝግቤያለሁ በሚል በሀገሪቱ ሕዝብ ላይ በአንድ ፈላጭ ቆራጭ የፓርቲ መዋቅር የሚያደርሰውን በደል ለመሸፋፈን እየሞከረ መሆኑን በአለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቀው ጸሃፊ ግራህም ፒብልስ ገለጸ።

ጸሀፊው ጉዳዩን አስመልክቶ ባቀረበው ሃተታ እንደገለጸው ዓለም ዓቀፍ መገናኛ ብዙሃንና ምእራባውያን ኢትዮጵያን የተሻለ የኢኮኖሚ እድገት አስመዝግባለች በሚል የሚያቀርቡት ሪፖርት የአገዛዙን ግፍና በደል ለመሸፈን ምክንያት ሆኗል።

በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያውያን በሀገራቸው ባለው የአንድ ፓርቲ አገዛዝ ግፍና በደል በመሰቃየታቸውና በኑሮ ውድነት በመማረራቸው በኢትዮጵያ ተመዝግቧል የሚባለው የኢኮኖሚ እድገት ለነሱ ምናቸውም አይደለም ብሏል — ታዋቂው ጸሃፊ ግራሃም ፒብልስ በሀተታው።

በኢትዮጵያ ተመዘገበ የተባለው የኢኮኖሚ እድገት እንደ ቢቢሲና ሲ ኤን ኤን ባሉ አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ሽፋን እያገኘ መሆኑን ታዋቂው ጸሀፊ ግራሃም ፒብልስ ይገልጻል።

የአለም ባንክን የመሳሰሉ አለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማትና የምዕራባውያን ሀገራትም ኢትዮጵያን በአፍሪካ የመረጋጋትና የሰላም አካባቢ በማለት ሲያወድሷት በመኖራቸው ስለ ሀገሪቱ የተለየ ገጽታ ለመስጠት መሞከሩንም ሀተታው አስፍሯል።
እውነታው ግን ይላል ግራሃም ፒብልስ በኢትዮጵያ ያለው እውነታ ግን የተለየና በኢኮኖሚ እድገት ሽፋን ስም አሰቃቂና ከፍተኛ በደል የሚታይበት ነው ብሏል።

በሰብአዊ መብት አያያዝ፣በዲሞክራሲና በሚዲያ ነጻነት እንዲሁም የዜጎች የነጻነት ሁኔታ በሚታይበት ጊዜ ኢትዮጵያ በአንድ ፈላጭ ቆራጭ አመራር ስር የወደቀች ፥ ሕዝብ የሚገደልባትና አሰቃቂ ተግባሮች የሚፈጸሙባት ሀገር መሆኗን መገንዘብ ይቻላል ነው ያለው።

ይህንንም ሲያስረዳ የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች በግፍ እንደሚታሰሩና እንደሚገደሉ፣ማንኛውም የተለየ ሀሳብ ያለውም በተለያዩ የሕግ ሽፋኖች እንደሚከሰስ በመግለጽ በሀገሪቱ ያለውን አስቸጋሪ ሁኔታ ጠቅሷል።

ግራሃም ፒብልስ በዚሁ ጽሁፉ እንዳለው ማንኛውም የተለየ ሀሳብ የሚያራምድ ሰው በአሸባሪነትና በጸረ ሰላምነት ይፈረጃል፥ በዚሁ ሳቢያም ተከሶ ወሕኒ ይወርዳል።
ተቋማትም በመንግስት ቁጥጥር ስር ካልሆኑ በስተቀር በነጻነት መስራት እንደማይችሉ በጽሁፉ አስረድቷል።

እናም አሁን ያለው የኢትዮጵያ ሁኔታ ዜጎችን ያስመረረና በስቃይ ውስጥ የከተተ አገዛዝ ያለበት መሆኑን ያሳያል ሲል ጸሀፊው ይናገራል።

የኢትዮጵያ ሁኔታም ምዕራባውያን እንደሚሉት የተረጋጋና የተሻለ ሳይሆን የግጭትና የትርምስ አካባቢ እየሆነ መጥቷል ሲል ግርሃም ፒብልስ ጽሁፉን ይደመድማል።