በኢትዮጵያ ያለው መንግስት በሙስና የተዘፈቀ ጨካኝና የዘረፋ መጠኑም ድንበር የማይገታው ነው ተባለ

(ኢሳት ዜና -ሐምሌ 20/2009) በአሜሪካ የህግ መወሰኛ ምክር ቤት የካሊፎርኒያ ተወካይ የሆኑት ዳና ሮራባከር እንዳሉት እሳቸው በግል የሚያውቋቸው ትውልደ ኢትዮጵያውያን የመንግስት ደጋፊ ባለመሆናቸው ብቻ ንብረታቸው እንደተወረሰ አስታውሰው እንዲህ ያለ የሰብአዊ መብትን ቀርቶ የግል ንብረትን እንኳ የማያከብር አገዛዝ ከአሜሪካ መንግስት ጋር ወዳጅና ተባባሪ ለመሆን መሞከሩ በጣም ይገርመኛል ብለዋል።

ባጭሩ አሉ የምክር ቤቱ አባል በኢትዮጵያ ያለው አገዛዝ ፈላጭ ቆራጭና ለምንም ነገር ገደብ የሌለው ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ የተረቀቀው የዚህ ህግ ዋና አርቃቂ የሆኑት የኒውጀርሲው ተወካይ ክሪስ ስሚዝ በበኩላቸው በኢትዮጵያ እየቀጠለ ያለው የሰብአዊ መብት ጥሰት በፍጹም ተቀባይነት የሌለው ነው ብለዋል።

ካለፍርድ ቤት ትእዛዝ መታሰር፣ግድያ፣ሰቆቃ በተቃዋሚ ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞች ላይ እየቀጠለ ነው ብለዋል።

ክሪስ ስሚዝ እንዳሉት በቅርቡ ለአንድ  አሁን በአሜሪካ ለሚገኝ ኢትዮጵያዊ አትሌትን ጉዳይ በተመለከተ ለአሜሪካ የዜግነትና ስደተኞች ጉዳይ ቢሮ የድጋፍ ደብዳቤ መጻፋቸውንና ጥያቄያቸውም ደምሰው አበበ የተባለው ሯጭ ቤተሰቦች ወደ አሜሪካ መጥተው እንዲያገኙት ነው ብለዋል።

ደምሰው ተቃዋሚ በመሆኑ ብቻ ተይዞ ውስጥ እግሩ ክፉኛ ተገርፎ እንዳይሮጥ የተደረገና ሌሎች ከፍተኛ ሰቆቃዎች የተፈጸመበት ግለሰብ ነው ብለዋል።

ሚስተር ስሚዝ ሲቀጥሉም አባ ጉያ የተባለ የአካል ጉዳተኛና የሀገሪቱ የአካል ጉዳተኞች ማህበር መሪን ትቃወመናለህ በሚል የአገዛዙ ደህንነቶች በእስር ካሰቃዩት በኋላ ደብድበው ጫካ ውስጥ ጥለውት በበጎ አድራጊዎች እርዳታ ከሞት መትረፉን ተናግረዋል።

አባ ጉያም ከአራት ወር በፊት በዚህ ምክር ቤት ቀርቦ ምስክርነት መስጠቱን አስታውሰዋል።

ይህ የተረቀቀው ህግ አሉ ሚስትር ስሚዝ በኢትዮጵያ ያለው አገዛዝ እንደ መስታወት ራሱን የሚያይበትና ለለውጥም እራሱን የሚያዘጋጅበትን እድል ይፈጥርለታል።

ኤች አር 128 በሚል ምህጻረ ቃል የሚጠራው ረቂቅ ህግ የአሜሪካ የህግ መወሰኛ ምክር ቤት በኢትዮጵያ ያለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲነሳ፣የታሰሩ የሰብአዊ መብት አቀንቃኞች፣ጋዜጠኞችና የተቃዋሚ መሪዎች እንዲፈቱ፣ህገ መንግስታዊ መብታቸውን በመጠቀማቸው ብቻ ለሞትና ለስቃይ የተዳረጉ ሰዎች ጉዳይ እንዲታይና የድርጊቱ ፈጻሚዎችም ለፍርድ እንዲቀርቡ ይጠይቃል።

ህጉ በተጨማሪም በኢትዮጵያ እየተፈጸመ ያለው የሰብአዊ መብት ጥሰት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት በኩል እንዲጣራ ይጠይቃል።

ረቂቅ ህጉ በሌሎች የምክር ቤቱ አባላት ዛሬ የድጋፍ አስተያየት ተሰጥቶበታል።ለምክር ቤቱም ተመርቶ በቅርቡ እንድሚጸድቅ ይጠበቃል።