በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳሩ ካልሰፋ ሀገሪቱ አደገኛ ሁኔታ ውስጥ ልትገባ ትችላለች ተባለ

(ኢሳት ዜና–መስከረም 9/2010) በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳሩ ካልሰፋ ሀገሪቱ አደገኛ ሁኔታ ውስጥ ልትገባ እንደምትችል የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ኮሚሽነር አስጠነቀቁ።

ኮሚሽነሩ ዛይድ ራድ አልሁሴን በዋሽንግተን ዲሲ ከሰብአዊ መብት ማህበረሰብ አባላትና ከጋዜጠኞች ጋር ባደረጉት ውይይት እንደገለጹት ኢትዮጵያውያን መብታቸው ካልተከበረና የፖለቲካ ምህዳሩ ካልሰፋ በሀገሪቱ የከፋ ቀውስ ሊከሰት ይችላል።

የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ኮሚሽነሩ ዛይድ ራድ አልሁሴን በኢትዮጵያ ባለፈው አመት የተቀሰቀሰውን ሕዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ የደረሰውን የሰብአዊ መብት ረገጣ ለመገምገም ወደ ኢትዮጵያ አምርተው እንደነበር አስታውሰዋል።

በዚሁም በኢትዮጵያ ያለው አገዛዝ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች የተፈጸመውን የሰብአዊ መብት ጥሰት ለመታዘብ እሳቸውና ቡድናቸው ወደ አካባቢው ለመጓዝ ጠይቀው በአገዛዙ መከልከላቸውን ገልጸዋል።

በዛን ጊዜም ከአገዛዙ ባለስልጣናትና ከተቃዋሚዎች ጋር ቢወያዩም ቡድናቸው ችግሩ ተፈጥሮባቸው ወደነበሩት አካባቢዎች ግን ለመጓዝ ፈቃድ አላገኘም ነው ያሉት።

እንደፈረንጆቹ አቆጣጠር በጥር 2018 ወደ ኢትዮጵያ እንደሚያመሩና ቡድናቸው ወደ ተፈለገው አካባቢ እንዲንቀሳቀስ በድጋሚ እንደሚጠይቁ ኮሚሽነሩ ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ ግልጽነት ከሌለና የፖለቲካ ምህዳሩ ካልሰፋ ሀገሪቱ አደገኛ ሁኔታ ላይ ልትወድቅ እንደምትችልም አስጠንቅቀዋል።

እንደ ኮሚሽነሩ ገለጻ ኢትዮጵያውያን ሰብአዊ መብታቸው ሊከበርላቸው ይገባል።

ይህ ካልሆነ ግን በሀገሪቱ የከፋ ቀውስ ሊፈጠር እንደሚችልና ይህም ለትልቅ ውድቀት እንደሚዳርግ በስልጣን ላይ ያሉት ገዥዎች ሊገነዘቡት ይገባል ብለዋል።–የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ኮሚሽነሩ ዛይድ ራድ አልሁሴን።