በኢትዮጵያ የአህያ እርድና የስጋ ሽያጭ እንደገና መቀጠሉ ታወቀ

(ኢሳት ዜና –ሐምሌ 24/2009)በኢትዮጵያ በህዝብ ተቃውሞ ተቋርጧል ተብሎ የነበረው የአህያ እርድና የስጋ ሽያጭ እንደገና መቀጠሉ ታወቀ።
በደብረዘይት ከተማ ተገንብቶ የአህያ እርድ ሲያካሂድ የነበረው ቄራ በህዝብ ቅሬታ ስራውን አቁሟል ከተባለ በኋላ ሰሞኑን 250 ሺ ኪሎግራም ስጋ ወደ ቬትናም ለመጀመሪያ ጊዜ ልኳል።
የቻይና እንደሆነ የሚታወቀው ሻን ዶንግ ዶንግ የተባለው ኩባንያ በቀን 2 መቶ አህዮችን በማረድ ስጋቸውን ወደውጭ ለመላክ መቋቋሙ ይታወቃል።
በ80 ሚሊየን ብር ካፒታል ይተቋቋመው ይሄው የአህያ ቄራ ከዛሬ 4 ወራት በፊት ከሕዝብ በተነሳ ተቃውሞ ስራውን አቁሟል ተብሎ ነበር።
ይሁንና ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ እርዱን በመቀጠል 250 ሺ ኪሎግራም የአህያ ስጋ ወደ ቬትናም ሰሞኑን መላኩን ፎርቹን ጋዜጣ ዘግቧል።
የአህያ እርዱና ቄራው ከ4 ወራት በፊት በኢትዮጵያ ከሃይማኖት ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ቁጣን በመቀስቀሱ ለጊዜው መንግስት እንዲቆም ተደርጓል ብሎ ነበር።
አሁን ግን ቁጣው ከበረደና የአህያ እርዱን አቁሜያለሁ ካለ በኋላ ኩባንያው ስራውን እንዲቀጥል የተደረገው በምን ምክንያት እንደሆነ ለማወቅ አልተቻለም።