በኢትዮጵያ የተከሰተው የድርቅ አደጋ ተባብሶ መቀጠሉን ዩኒሴፍ አስታወቀ::

ሰኔ ፲፭( አሥራ አምስት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ከአንድ ዓመት በላይ የዘለቀው የምስራቅ አፍሪካ አገራት ድርቅን ተከትሎ በኢትዮጵያ የምግብ ዋስትና እየተመናመነ መምጣቱን የተባበሩት መንግስታት የህጻናት አድን ድርጅት-ዩኒሴፍ አስታውቋል።
በተለይ በምስራቅ ኢትዮጵያ የተባባሰው ድርቅ የቤት እንስሳትን ክፉኛ እየጨረሰ ሲሆን፤ የአካባቢው ነዋሪዎች ከመኖሪያ ቀያቸው እንዲፈናቀሉና በየመጠለያ ጣቢያዎችእንዲጠለሉ አድርጓቸዋል።
ድርቁ በፈጠረው ርሃብ ምክንያት በተለይ በደረቃማ የአየር ንብረት የሚኖሩት የኦጋዴን ነዋሪዎች ሕይወት መቃወሱን የረድኤት ድርጅቶች አስታውቀዋል። እንደ ዩኒሴፍ ገለጻ ቁጥራቸው ከ7 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን ዜጎች ሕይወታቸውን ለማቆየት አሁንም እለታዊ እርዳታ ጠባቂዎች ሆነዋል።
ዓለምአቀፍ ለጋሾች ወቅታዊ ምላሽ ባለመስጠታቸውና በአገሪቱ ያለው የምግብ ክምችት እየተመናመነ በመምጣቱ የርሃቢ ተጠቂዎች ላይ ሰብዓዊ ቀውስ ሊፈጠር ይችላልሲል ዓለምአቀፉ የሕጻናት አድርን ድርጅት ስጋቱን ገልጽዋል።
በአንድ ብቸኛ አንባገነናዊ ስርዓት የምትመራው ኢትዮጵያ ሕዝባዊ ቁጣው እያየለ መምጣቱ የረድኤት ድርጅቶች ለርሃብተኞች የሚሰጡት እርዳታ ላይም ሳንካ ፈጥሯል።ደቡባዊ ምስራቅ ኢትዮጵያ ነዋሪ ለሆኑ አርብቶ አደሮች ወቅታዊ የምግብ እርዳታ ካልቀረበላቸው አደጋው የከፋ ሊሆን ይችላል ሲል ተመድ አስጠንቅቋል።
በዚሁ በምሥራቅ ኢትዮጵያ በውል የቦታው ስም ያልታወቀ በድርቅ ሳቢያ ለረሃብ ተጋልጠው ህይወታቸው ሞት አፋር የደረሱ ነዋሪዎች “አምላክ ሆይ ማለቃችን ነው! አንተው ድረስልን!” እያሉ ሲማጸኑ ተስተውለዋል።
ድርቅ ለረሀብ መንስኤ ሊሆን እንደማይችል በታመነበት በአሁኑ ወቅት ላለፉት አስራ ሁለት ዓመታት ያለማቋረጥ 11 በመቶ የኢኮኖሚ እድገት አስመዝግቤያለሁ እየተባለ በቆየበት ሀገር የአንድ ወቅት ዝናም መዘግየቱን ተከትሎ ዜጎች በዚህ ደረጃ መገኘታቸው ብዙዎችን እያነጋገረ ነው።