በኢትዮጵያ የሚታየው ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ትኩረት ካልተሰጣቸው አሁን እየታዩ ያሉ ችግሮች ሊፈቱ እንደማይችል ተገለጸ

ኢሳት (መጋቢት 20 ፥ 2009)

ከኢትዮጵያ እየጨመረ የመጣን የስደተኞች ቁጥር ለመግታት በሃገሪቱ ያሉ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ በግጭቶች ዙሪያ የሚሰራ አንድ አለም አቀፍ ተቋም አሳሰበ።

ወደ አንድ መቶ ሚሊዮን አካባቢ የሚጠጋ ህዝብ ያላት ኢትዮጵያ ከጥቂት አመታት ወዲህ ጀምሮ ለአለም ስደተኞች ቁጥር መበራከት ምንጭ እየሆነች መምጣቷን አርምድ ኮንፍሊክትስ የተሰኘውና በአለም ባሉ ግጭቶች ዙሪያ የሚሰራው ተቋም የኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይን አስመልክቶ ባወጣው ሪፖርት አመልክቷል።

በየአመቱ አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን የሆኑ 15ሺ አካባቢ ስደተኞች ወደ ደቡብ አፍሪካ ብቻ ይሰደዳሉ ያለው ድርጅቱ፣ በኢትዮጵያ ተንሰራፍቶ የቀጠለው ፖለቲካዊ ውጥረት እንዲሁም የኢኮኖሚ ተጠቃሚ አለመሆን ለስደተኞቹ መበራከት ምክንያት ለመሆኑ ይፋ አድርጓል።

በሃገሪቱ ላለው ለዚሁ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ትኩረት መስጠት ይገባል ሲል ያሳሰበው አርምድ ኮንፍሊክትስ ተቋም፣ ችግሩ መፍትሄን ሲያገኝ ብቻ የስደተኞቹ ፍልሰት ሊቀንስ እንደሚችል አስረድቷል።

በሃገሪቱ በአለም ካሉ ሃገራት ምሳሌ የሚሆን የኢኮኖሚ ችግሮች ትኩረት መስጠት ይገባል ሲል ያሳሰበው አርምድ ኮንፍሊክት ተቋም፣ ችግሩ መፍትሄን ሲያገኝ ብቻ የስደተኞቹ ፍልሰት ሊቀንስ እንደሚችል አስረድቷል።

የኢትዮጵያ መንግግስት በአለም ካሉ ሃገራት ምሳሌ የሚሆን የኢኮኖሚ እድገትን አስመዝግቤያለሁ ቢልም፣ አሁም ድረስ ወደ 20 ሚሊዮን አካባቢ የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን ከድህነት ጠለል በታች እንደሚገኙ አለም አቀፍ ድርጅቶቹ በሪፖርቱ አቅርቧል።

ባለፈው አመት በተለይ በኦሮሚያ ክልል የተቀሰቀሰው ህዝባዊ ተቃውሞ ለበርካታ ሰዎች መሰደድ ምክንያት መሆኑን ያወሳው አርምድ ኮንፍሊክትስ ድርጅት፣ ችግሩ አሁንም ድረስ ዕልባት ባለማግኘቱ በበርካታ የሃገሪቱ አካባቢዎች ውጥረት መቀጠሉን ገልጿል።

በስልጣን ላይ ያለው ገዥው የኢህአዴግ መንግስት ቁርጠኛ የሆነ የፖለቲካ ድርድርን ለማድረግ ዝግጁ ባለመሆኑ ከሃገሪቱ የሚሰደዱ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ሊሄድ እንደሚችል ስጋቱን አስቀምጧል።

በሃገሪቱ ቀጥሎ ያለው ፖለቲካዊ ውጥረትና አለመረጋጋት በተለይ በኦሮሞ ብሄር ተወላጆች ላይ የከፋ ችግርን እያስከተለ እንደሚገኝ የገለጸው ተቋሙ በፈረንጆቹ ጥር ወር 2017 አም ወደ የመን ከተሰደዱ ኢትዮጵያውያን መካከል 89 በመቶ የሚሆኑት የዚሁ ብሄር ተወላጅ እንደሆኑም አመልክቷል።

የአለም አቀፍ ስደተኞች ድርጅት (IOM) በፈረንጆቹ 2016 አም ብቻ ጦርነት ዕልባት ወዳላገኘባት የመን ወደ 90ሺ አካባቢ ኢትዮጵያውያን መሰደዳቸውን ይፋ ማደረጉ ይታወሳል። የተለያዩ የስደተኛ ድርጅቶች ኢትዮጵያውያኑ ጦርነት ወዳለባት የመን የመሰደዳቸው ጉዳይ ስጋት እያሳደረ መምጣቱን በተደጋጋሚ ሲገልፁ ቆይተዋል።

ከኢትዮጵያ በከፍተኛ መጠን በመሰደድ ላይ ያሉ ስደተኞች ወደ ጎረቤት ኬንያ፣ ጅቡቲ፣ ግብፅ፣ ሶማሊያ፣ እና ሱዳን በኩል በማድረግ ወደ ተለያዩ የአረብ ሃገራትና አውሮፓ እንዲሁም ደቡብ አፍሪካ የመጓዝ እቅድ እንዳላቸው ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ መንግስት በቅርቡ ከአውሮፓ ህብረት ጋር የስደተኞቹ ቁጥር በሚቀንስበት ሁኔታ ላይ በጋራ ለመስራት ስምምነት ቢደርስም በሃገሪቱ ያሉ የፖለቲካ ውጥረቶች ትኩረት ሳይሰጣቸው መቅረቱንና ችግሩ ቀጥሎ እንደሚገኝ አርምድ ኮንፍሊክት ተቋም በሪፖርቱ አስፍሯል። አለም አቀፍ የልማት አጋሮች በኢትዮጵያ የስራ አጥነት ቁጥርን ለመቀነስ የሚሰጡት ድጋፍ በአግባቡ ጥቅም ላይ ስለመዋሉ ማረጋገጫ ሊኖር ይገባል ሲልም ድርጅቱ አሳስቧል።

ካለፉት ጥቂት አመታት ወዲህ  በርካታ ኢትዮጵያውያን ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመግባት በሚያደርጉት ጥረት በተለያዩ የደቡባዊ አፍሪካ ሃገራት ወደሃገሪቱ በህገወጥ መንገድ ገብታችኋል ተብለው ለእስር ሲዳረጉ መቆየታቸው ይታወሳል።

በማላዊ፣ ታንዛኒያ፣ ዚምባብዌ፣ ኬንያ፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በእስር ላይ እንደሚገኙ የአለም አቀፍ ስደተኞች ድርጅት (IOM) መረጃ ያመለክታል።