በኢትዮጵያ ዘረፋ ከሚፈጸምባቸው መስኮች አንዱ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መሆኑ ተገለጸ

(ኢሳት ዜና–ነሐሴ 2/2009) በኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ ከሚባክንባቸውና ዘረፋ ከሚፈጸምባቸው መስኮች አንዱ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መሆኑን የኢሳት ምንጮች ገለጹ።
በተለይ ለባለስልጣናት የውጭ ሀገር ጉዞ በሚል ንግድ ባንክ የሚሰጠው ቪዛ ካርድ ሒሳቡ የማይወራረድ በመሆኑ ለከፍተኛ ብክነት ተጋልጧል።
ለአንድ ጉዞ ለአንዳንዶች ከህግ ውጪ እስከ አንድ መቶ ሺ ዶላር እንድሚሰጣቸውም ምንጮች ገልጸዋል። በቪዛ ካርድ ከፍተኛ ገንዘብ በመውሰድ ከሚጠቀሙ ባለስልጣናት አንዱና ግንባር ቀደሙ ዶክተር አርከበ እቁባይ መሆናቸውን የገለጹት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ምንጮች የባንኩ ፕሬዝዳንት አቶ በቃሉ ዘለቀ ለሒደቱ ዋና ተባባሪ መሆናቸውንም ያስረዳሉ።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለባለስልጣናቱ የሚያዘጋጀውን ቪዛ ካርድ ይዘው ከሀገር የሚወጡት ባለስልጣናት ባለ 5 ኮከብ ሆቴል ከማረፍ ጀምሮ በልዩ ልዩ አላስፈላጊ ወጪ ገንዘቡን በማባከን በሳምንት ጊዜ ውስጥ ጨረስን ብለው እንደገና የውጭ ምንዛሪ እያስሞሉ እንደሚጠቀሙም ተመልክቷል።
ዋና ለሚባሉት ባለስልጣናት ለነ አቶ አርከበ እቁባይ በአንድ ጊዜ የሚሞላው እስከ አንድ መቶ ሺ የአሜሪካን ዶላር እንደሆነም ታውቋል።ከጉዞ ሲመለሱም ሒሳቡ ስለማይወራረድ ሰስፔንስ በሚል እንደሚታለፍም ተመልክቷል።
ቪዛ ካርዱን በውጭ ሀገር ምንዛሪ እየሞላ ለባለስልጣናቱ የሚያመቻቸው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቶ በቃሉ ዘለቀ ሳይወራረድ ለሚባክነው ወይንም ወደ ባለስልጣናቱ ለሚዛወረው የውጭ ምንዛሪ ርሳቸው በምትኩ ከሕወሃት ባለስልጣናት ከለላ እንደሚፈልጉም ያስረዳል።
በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ውስጥ በሚካሄደው መጠነ ሰፊ ሙስና የቀድሞው የቦርድ ሊቀመንበርና የአሁኑ የቦርድ አባል አቶ አባይ ጸሐዬና ወንድማቸው አቶ ልኡል ጸሓዬ ዋና ተዋናይ ሆነው መቆየታቸውን የሚገልጹት ምንጮች አቶ በቃሉ ዘለቀም በነርሱ ከለላ የራሳቸውን ድርሻ ሲወስዱ መቆየታቸውን ያስረዳሉ።
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ከመሞታቸው በፊት አቶ አባይ ጸሃዬን በአቶ በረከት ስምኦን በመተካት አቶ አባይ ጸሃዬን በቦርድ አባልነት ብቻ እንዲቀጥሉ ቢያደርጉም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ውስጥ አሁንም የመሪነቱን ስፍራ የሚጫወቱት አቶ አባይ ጸሃዬ መሆናቸውን ምንጮቹ ይገልጻሉ።
የባንኩ የውጭ ምንዛሪ ክፍል ውስጥ ዋና ተዋናይ የነበሩት የአቶ አባይ ጸሃዬ ወንድም አቶ ልኡል ጸሃዬ ወደ ሶማሌላንድ ሀርጌሳ መዛወራቸውን ምንጮቹ አመልክተዋል።