በኢትዮጵያ ውስጥ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 12 መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ከስራቸው ታገዱ

ኢሳት (ጥቅምት 18 ፥ 2009)

በኢትዮጵያ ባለፉት ሶስት ወራቶች ውስጥ ከተቋቋሙበት አላማ ውጭ ሲንቀሳቀሱ ነበሩ የተባሉት 12 መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ከስራቸው ታገዱ።

ከአራት አመት በፊት አጨቃጫቂ ነው የተባለው የበጎ አድራጎት ድርጅቶችን የሚቆጣጠረው አዋጅ ተግባራዊ ከተደረገ በኋላ በየጊዜው ቁጥጥር እየተደረገባቸው ከስራቸው የሚደረጉ ሃገር በቀልና የውጭ ድርጅቶች ቁጥር እየጨማረ መምጣቱም ታውቋል።

የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ኤጀንሲ የስራ ፈቃዳቸው የታገደባቸው ተቋማት ፈቃድ ሲያወጡ እንሰራለን ካሉት ስራ ውጭ ሲንቀሳቀሱ በመገኘታቸው ነው ሲል ለሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል።

ይሁንና ድርጅቶቹ በምን አይነት ስራ ውስጥ ሲንቀሳቀሱ እንደነበርና የሃገር ውስጥ አሊያም የውጭ ይሁኑ መንግስት ዝርዝር መረጃን ከመስጠት ተቆጥቧል።

አንዳንድ ድርጅቶች ከውጭ እንደመቋቋቸው የውጭ ተቋማት ተልዕኮ ለማስፈጸም ይሞክራሉ ሲሉ የኤጀንሲው ባለስልጣናት አስታውቀዋል።

ባለፉት ሶስት ወራቶች ውስጥ ብቻ ከተቋቋሙበት አላማ ውጭ ሲንቀሳቀሱ ነበሩ የተባሉ ድርጅቶችን በስም ያልጠቀሰው መንግስት ከታገዱት የበጎ አድራጎት ተቋማት በተጨማሪ ከስድስት ድርጅቶች የመጀመሪያና የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ መሰጠቱም ተነግሯል።

የኢትዮጵያ መንግስት የበጎ አድራጎት ድርጅቶችን እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር ያወጣውን አዋጅ ተከትሎ አሜሪካንን ጨምሮ የተለያዩ ሃገራት ዕርምጃው የተቋማቱን ስራ ለመከታተል እንደሆነ ስጋታቸውን ሲገልጹ ቆይተዋል።

የአዋጁ መተግባርን ምክንያት በማድረግ ከ100 የሚበልጡ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ስራቸውን እንዳቋረጡ የሚታወስ ነው።