በኢትዮጵያ ከ9.2 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ለውሃ እጥረት ተጋላጭ ሆነዋል ሲል ዩኔሴፍ አታወቀ

መጋቢት ፲፰ (አሥራ ስምንት)ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በህንድ ውቂያኖስ ባህር ሙቀት ምክንያት በተከሰተው የምስራቅ አፍሪካ አገራት ድርቅ ምክንያት በተለይ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ከ9.2 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ለውሃ ጥም ተጋላጭ መሆናቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የህጻናት አድን ድርጅት ፣ ዩኒሴፍ /UNICEF/ በሪፖርቱ አስታወቀ። ድርቁ በሶማሊያ፣ደቡብ ክልል እና ኦሮሚያ በከፋ ሁኔታ ተባባሶ ቀጥሏል።
የበልግ ዝናብ ባልጣለባቸው በሶማሊያ፣ ደቡብ ክልል፣ በትግራይ፣ አፋር እና ኦሮሚያ ክልሎች ለ839 ሺህ 500 ለሚሆኑ ነዋሪዎች የውሃ እደላ መጀመሩንም ዩኔሴፍ /UNICEF/ ቢያመለክትም፣ 90 ከመቶ በላይ ለሚሆኑት ዜጎች ንጹህ የመጠጥ ውሃ እና የጤና አገልግሎት አቅርቦት በበቂ ሁኔታ ማዳረስ አልተቻለም ብሎአል።
በተጨማሪም በደቡብ ኦሞ ዞን መና ጻማ ወረዳ አርብቶ አደሮች በድርቁ ምክንያት ግጦሽ እና ውሃ በማጣታቸው ከ60 ከመቶ በላይ የቤት እንስሶች ያለቁባቸው ሲሆን፣ በህይወት ያሉትም ቢሆን በአስጊ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ታውቋል። አብዛሃኛው በዞኑ የሚገኙ የጤና ተቋማት እና ትምህርት ቤቶች ውስጥ የውሃ አገልግሎት የለም። ነዋሪዎች 20 ሊትር የሚይዝ አንድ ጀሪካን ውሃ እስከ 5 ብር ለመግዛት የተገደዱ ሲሆን፣ ድርቁ ከዚህ የከፋ እልቂት በዜጎች ላይ ከማስከተሉ አስቀድሞ በአፋጣኝ ሕይወታቸውን መታደግ ይገባል ሲል ዩኒሴፍ አስጠንቅቋል።