በኢትዮጵያ ከመንገድ ግንባታ ጋር ተያይዞ የሚጣሉ መርዛማ ቆሻሻዎች ለሕጻናት ሞት ምክንያት እየሆኑ ነው ተባለ

(ኢሳት ዜና–ነሐሴ 19/2009)በኢትዮጵያ ከሚገነቡ አዳዲስ መንገዶች ጋር ተያያዞ የሚጣሉ መርዛማ ቆሻሻዎች ለሕጻናት ሞት ምክንያት እየሆኑ መምጣታቸውን አንድ ጥናት አመለከተ።

ጥናቱን ያካሄዱት ከለንደንና ደብሊን ከሚገኙ ሁለት ዩኒቨርስቲዎች የመጡ ባለሙያዎች ናቸው።

ከለንደንና ደብሊን እንደተውጣጡት ባለሙያዎቹ ገለጻ አዳዲስ መንገድ በሚገነባባቸው የኢትዮጵያ አካባቢዎች በሕገወጥ ሁኔታ የሚጣሉ መርዛማ ቆሻሻዎች ለሕጻናት ሞት ምክንያት ናቸው።

በተለይ ደግሞ አዲስ በሚገነቡ መንገዶች በ5 ኪሎሜትሮች ዙሪያ የሚኖሩ እናቶች ሕጻናት ወልደው ከሆነ ከመርዛማ ቆሻሻው ጋር በተያያዘ ሕይወታቸውን ያጣሉ።

ከዊን ሜሪ ከተባለ የለንደን ዩኒቨርስቲና ትሪኒቲ ኮሌጅ ከተባለ የደብሊን ተቋም የተውጣጡት ባለሙያዎች ያገኙትን ጥናት ይፋ ሲያደርጉ እንደገለጹት በ5 ኪሎሜትሮች ውስጥ ባሉ አዳዲስ የመንገዶች ግንባታ በሚካሄድባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ህጻናት በመርዛማ ቆሻሻ የመሞታቸው እድል ከሌሎቹ በ3 በመቶ ይጨምራል።

የእነዚህ ህጻናት የመሞት እድል 8 ነጥብ 5 በመቶ ሲሆን የሌሎቹ ደግሞ 11 ነጥብ 5 በመቶ ነው።
በዚሁ መርዛማ ቆሻሻ ምክንያት እድሜያቸው ከ5 በታች የሆኑ ህጻናት የሆሞግሎቢን ንጥረ ነገር እጥረት ስለሚገጥማቸው በደም ማነስ ችግር እንደሚሰቃዩና በዚሁም ሳቢያ እንደሚሞቱ ጥናቱ አመልክቷል።

ተመራማሪዎቹ ጥናቱን በኢትዮጵያ ያደረጉት በሐገሪቱ የመንገድ ግንባታ በመበራከቱ ነው ተብሏል።ዘገባው የኒው ሜዲካል ኔት ነው።