በኢትዮጵያ አፋጣኝ የምግብ እርዳታ የሚፈልጉና በርሃብ የተጠቁት ዜጎች ቁጥር ሊያሻቅብ እንደሚችል ተዘገበ

ግንቦት ፲፮ ( አሥራ ስድስት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ፊውስ ኔት ፣ በኢትዮጵያ የተከሰተው ረሃብ ወደ አሳሳቢ ደረጃ እንደሚደርስና የምግብር እርዳታ የሚሹ ወገኖች ቁጥር ከዚህ በፊት ከተገለጸው እንደሚጨምር ዘግቧል። በቅርቡ 7 ሚሊዮን 700 ሰዎች አፋጣኝ የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ተገልጾ ነበር።
ድርቁ የቤት እንስሳትን ማውደሙን፣ የሚጥለው ዝናብ አስተማማኝ አለመሆኑንና የሚላከው እርዳታም በቂ አለመሆኑን የተመድ የመረጃ መረብ ገልጿል። በኢትዮጵያ ከሚያዚያ መጨረሻ እስከ ግንቦት መግቢያ የተጠናከረ ዝናብ ቢዘንብም ፣ ውጤቱ ግን ዝቀተኛ እንደሚሆን አሜሪካ የሚገኘው የረሃብ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ኔትወርክ ገልጿል።
በሚቀጥሉት 3 ወራት በደቡብ ምስራቅ የሚገኙ አርብቶአደሮች በከፍተኛ ሁኔታ የሚጎዱ ሲሆኑ፣ የችግሩ ደረጃው ወደ አራተኛ ደረጃ ከፍ እንደሚልና 5ኛ ደረጃ ላይ ከደረሰ ድርቁ ወደ ረሃብ ደረጃ እንደሚቀየር ተዘግቧል።
ከጥር እስከ ሚያዚያ በነበረው ጊዜ 5 ሚሊዮን 600 ሺ መራባቸው ከተነገረ በሁዋላ፣ ቁጥሩ ወደ 7 ሚሊዮን 700 ሺ ከፍ ያለ ሲሆን፣ ይህ አሃዝ በሰኔ ወር ላይ እንደሚጨምር ተመድ አስታውቛል።
የአለማቀፉ ማህበረሰብ አስቸኳይ እርዳታ እንዲያድርግም ተመድ ጠይቋል።