በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል 450 ሺ የሚጠጋ ህዝብ ወደ መጠለያ ካምፕ ገባ

(ኢሳት ዜና –ሐምሌ 13/2009)ዋሽንግተን ፖስት በጽሁፉ እንዳስነበበው በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ለሁለት ተከታታይ ወቅቶች በሶማሌ ክልል የዝናብ እጥረት ተከስቷል።

ይህ ደግሞ በሚሊየን የሚጠጉ የአካባቢው ነዋሪዎች የምግብ እርዳታ ጥገኞች እንዲሆኑና የቀድሞ የአኗኗር ዘይቤአቸውን እንዲቀየር አድርጎታል ይላል ዘገባው።

የጽሁፉ ዘጋቢ በመጠለያው ከሚገኙት የሱማሌ ተወላጆች ውስጥ ያናገራቸው ወይዘሮ ዘይነብ ጣሂር የድርቁ አስከፊነት በሳቸውና በቤተሰቦቻቸው ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን ይናገራሉ።

የዘጠኝ ልጆች እናት የሆኑት ወይዘሮ ዘይነብ ጣሂር ከችግሩ በፊት ከ350 በላይ በጎች ፣ፍየሎችና ሌሎች የቀንድ ከብቶች የነበራቸው ሲሆን ዝናብ በመጥፋቱ ምክንያት የቀንድ ከብቶቹ ግጦሽ አጥተው መሞታቸውን ይገልጻሉ።

ዝናብ ቢዘንብም እንኳን ምንም የቀንድ ከብቶች የሌላቸው በመሆኑ ወደ ትላንቱ ስራቸው መመለስ ፍላጎት እንደሌላቸው ነው የሚናገሩት።

ዘይነብ የወደፊት ህይወታቸውም ቢሆን አሳሳቢ ሁኔታ ላይ ወድቋል ይላሉ።

የአለም አቀፉ የምግብ ፕሮግራም ምክትል ዳይሬክተር ሳሚር ዋናሚ ለዋሽንግተን ፖስት እንደተናገሩት ችግሩን ለመቅረፍ በብዙ የአርብቶ አደር አካባቢዎች የአኗኗር ዘዬአቸው የሚፋጠንበት ሁኔታ ተፈጥሯል።

ይህ ደግሞ በየጊዜው ለሚፈጠረው ችግር መፍትሄ ሊሆን ይችላል ይላሉ ዳይሬክተሯ።

ከ5 ሚሊየን በላይ ህዝብ መኖሪያ የሆነው የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል 40 በመቶው አርብቶ አደር መሆኑን ዘገባው አመልክቷል።