በኢትዮጵያ ለወራት በዕስር ላይ የቆዩ ሶስት ግብጻውያን መለቀቃቸው ተገለጸ

ኢሳት (ጥር 4 ፥ 2009))

ግብጽ በኢትዮጵያ ለወራት በዕስር ላይ የቆዩ ሶስት ዜጎቿ መለቀቃቸውን ሃሙስ አስታወቀች። በኢትዮጵያ በተለያዩ የኦሮሚያ የክልል ከተሞች ሲካሄድ ከቆየው ህዝባዊ ተቃውሞ ጋር በተገናኘ ሶስቱ ግብጻውያን እጃቸው አለበት ተብሎ ለእስር መዳረጋቸው ይታወሳል። የግለሰቦቹን መታሰር ተከትሎ በሁለቱ ሃገራት መካከል ከሁለት ወር በላይ የፈጀ ድርድር ሲካሄድ ቆይቶ ሶስቱ ግብጻውያን ሊለቀቁ መቻላቸው አህራም የተሰኘው ጋዜጣ ዘግቧል።

ሶስቱ ግብጻውያን ረቡዕ ምሽት ከአዲስ አበባ ወደ ካይሮ ያቀኑ ሲሆን፣ በግለሰቦቹ ላይ ምንም አይነት ክስ አለመመስረቱንም የግብፅ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መገለጫ አውስቷል።

የሶስቱ ግብጻውያን መታሰርን ተከልትሎ የሃገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳም’ህ ሹክሪ በህዳር ወር መጨረሻ ላይ ወደ አዲስ አበባ በመጓዝ በጉዳዩ ዙሪያ ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋር መምከራቸው ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የግብፅ መንግስት ለተቃዋሚ ሃይሎች በተለይ ለኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ድጋፍን በማድረግ በሃገሪቱ ህዝባዊ ተቃውሞ እንዲቀጣጠል አስተዋጾ አድርጓል ሲል ይፋዊ ተቃውሞ ማሰማቱ ይታወሳል።

ይሁንና የግብፅ ውጭ ጉዳይ ሚኒስተር በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ሲል በገለጸው ችግር ምንም አይነት ጣልቃ ገብነት አለመፈጸሙንና የቀረበው ቅሬታ መሰረት የሌለው ነው ሲል ማጣጣሉ ሲዘገብ ቆይቷል።

የሃገሪቱ ፕሬዚደንት አብደል ፈታህ አልሲሲ ሃገራቸው መቼም ቢሆን በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እንደማትገባና ገብታም እንደማታውቅ መግለጻቸውን የግብጽ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

በአዲስ አበባ ለእስር ተዳርገው ከቆዩት ሶስቱ ግብጻውያን መካከል አንደኛው የራዲሰን ሆቴል አስራ አስኪያጅ የነበሩ ሲሆን ሁለቱ ደግሞ በተለያዩ ድርጅቶች ውስጥ ሲያገለግሉ እንደነበር ለመረዳት ተችሏል።

ይሁንና የግብፅ መንግስት ከወራት በኋላ ከእስር ስለተለቀቁት ዜጎቹ ማንነት የሰጠው ዝርዝር መረጃ የለም።

የግለሰቦቹን መታሰርም ሆነ መለቀቅ አስመልክቶ ከኢትዮጵያ በኩል እስካሁን ድረስ የተሰጠ መግለጫ አለመኖሩም ታውቋል። በሁለቱ ሃገራት መካከል የተፈጠረውን ዲፕሎማሲያዊ አለመግባባት ተከትሎ ኢትዮጵያና ግብፅ በአባይ ግድብ ግንባታ ዙሪያ ሲያካሄዱ የቆዩት ድርድር መቋረጡም የሚታወስ ነው።

በቅርቡ በአዲስ አበባ በሚካሄደው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ የግብፁ ፕሬዚደንት እንደሚታደሙና ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋር በተፈጠሩ አለመግባባቶች ዙሪያ ምክክርን ያካሄዳሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ለመረዳት ተችሏል።