በኢትዮጵያና ኬንያ ድንበር ስኳር ጭነው የቆሙት ከባድ ተሽከርካሪዎች ባለንብረቶች ችግር ውስጥ መውደቃቸውን ገለጹ

(ኢሳት ዜና–መስከረም 24/2010) በኢትዮጵያና ኬኒያ ድንበር ሞያሌ ላይ ከሁለት ወራት በላይ ስኳር ጭነው የቆሙት ከባድ ተሽከርካሪዎች ባለንብረቶች ከፍተኛ ችግር ውስጥ መግባታቸውን በተለይ ለኢሳት ገለጹ።

ከ100 በላይ የሚሆኑትና እያንዳንዳቸው 400ኩንታል ስኳር የጫኑት እነዚህ ተሽከርካሪዎች ለከፍተኛ ብልሽት እየተዳረጉ ሲሆን የጫኑት ስኳርም በመቅለጥ ላይ መሆኑን አስታውቀዋል።

በባንክ ብድር የገዟቸው ተሽከርካሪዎች ያለስራ ከሁለት ወራት በላይ በመቆየታቸው ለባንክ የሚከፍሉት ገንዘብ እንደሌላቸው የጠቀሱት ባለንብረቶቹ አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝን ለማነጋገር ያደረጉት ጥረትም እንዳልተሳካላቸው ገለጸዋል።
በሌላ በኩል የሕወሃት መንግስት ከአየን ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘ በሀገሪቱ ከፍተኛ የሆነ የስኳር እጥረት መከሰቱን ገልጿል።

መነሻቸው ወንጂ መዳረሻቸው ናይሮቢ ኬኒያ ነበር። ብራይት ድንበር ተሻጋሪ ከተሰኘ ማህበር ጋር ውል ፈጽመው ከ44ሺህ ኩንታል በላይ ስኳር ወደ ናይሮቢ ለመውሰድ የተስማሙት 110 ከባድ ተሽከርካሪ ባለንብረቶች፡ ከሁለት ወራት በፊት ጉዞ ይጀምራሉ። የኢትዮጵያን ድንበር ከማቋረጣቸው በፊት ሞያሌ ላይ ያልተጠበቀ ነገር ገጠማቸው። ወደፊት የማያስኬድ ባሉበት እንዲቆሙ የሚያደርግ ጉዳይ። ከቀረጥ ነጻ እንዲገባ የተፈቀደለት ስኳር ሞያሌ ላይ ተገታ።

ምክንያቱ በእርግጥ አልታወቀም። የሚቀበላችሁ ሰው ጠፍቷል የሚል መልስ ግን ይሰማሉ። ከቀረጥ ነጻ ይሆናል የተባለበት ጊዜ ገደብ በማለፉ እንዲገባ አልተፈቀደለትም የሚል ወሬም አለ።

የኬንያ መንገዶች ይህን ያህል ጭነት መሸከም የማይችሉ በመሆናቸው ጭነቱን ካልቀነሱ አይገቡም የሚል ምክንያትም ይነሳል።

ከየትኛውም የሁለቱ ሀገራት መንግስታት ትክክለኛው ምክንያት እስከአሁን አልታወቀም። መመለስ የማይቻል ሆነ። ወደፊት መቀጠልም ተከለከለ። ከ100 በላይ ከባድ ተሽከርካሪዎች መንገድ ዘግተው ከጫኑት ስኳር ጋር ለቀናት ፣ለሳምንታትና ለወራት ባሉበት እንዲቆሙ ተደረጉ።

ከወዲህም ከወዲያም መፍትሄ የሚሰጥ ያጡት ባለንብረቶች ለከፍተኛ ችግር መጋለጣቸውን ነው በተለይ ለኢሳት የገለጹት።

ጸሀይና ቅዝቃዜ እየተፈራረቁባቸው የሚገኙት ተሽከርካሪዎች የጫኑት ስኳር በመቅለጡ በንብረት ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ለከፍተኛ ኪሳራ እየዳረጋቸው እንደሆነም ገልጸዋል።

ኪሳራው ያለስራ በመቀመጣቸው ተበድረው ለገዟቸው ተሽከርካሪዎች የሚከፍሉት ገንዘብ እንዳይኖራቸው በማድረግ ህልውናቸው አደጋ ላይ መውደቁንም ባለንብረቶቹ ይናገራሉ።

ከ44ሺህ ኩንታል በላይ ስኳር የጫኑት ተሽከርካሪዎቹ በአሁኑ ሰዓት በመከላከያ ሰራዊት እየተጠበቁ ባሉበት ይገኛሉ። ባለንብረቶቹ መንግስት ጉዳዩን እልባት እንዲሰጠው ያደርጉት ሙከራ ሊሳካ አልቻለም።

አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝን ለማነጋገር ስድስት ተወካዮቻቸውን ቢልኩም እንዳልተፈቀደላቸው ገልጸዋል። መፍትሄ የሚሰጠን አጣን ሲሉም በምሬት ይናገራሉ።

በስልጣን ላይ ያለው መንግስት ባለፈው ዓመት በተያዘው 2010 መጀመሪያ አንስቶ ስኳር ወደ ውጭ መላክ እንደሚጀመር መናገሩ ይታወሳል።

በሀምሌ ወር ላይም ወደኬንያ ስኳር መላክ መጀመሩን የመንግስት መገናኛ ብዙሃን መግለጻቸው ይታወሳል።–ተላከ የተባለው ስኳር ሞያሌ ላይ ተገቶ ቀረ እንጂ።

ዛሬ የስኳር ኮርፖሬሽን በይፋ እንደገለጸው በኢትዮጵያ የስኳር እጥረት አጋጥሟል። ችግሩን በመደበቅ የቆየው መንግስት እጥረት መከሰቱን ባመነበት በዛሬ መግለጫው የእጥረቱን ምክንያት ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ማያያዙ አስገራሚ ሆኗል።

ከ77ቢሊየን ብር በላይ የተመደበለትና በህወሀት ጄኔራሎች በሚመራው ሜቴክ የተዘረፈውን ገንዘብ በመደበቅ ምክንያቱን በአየር ንብረት ላይ ማላከኩን ታዛቢዎች ይገልጻሉ።