በኢህአዴግ እና በመምህራን መካከል የተፈጠረው አለመግባባት እየተካረረ ነው

ሰኔ ፮ (ስድስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:- “ተቃዋሚ ናቸው” የተባሉ መምህራንን ከሥራቸው ለማባረር ለየትምህርት ቤቶች የወረደን መመሪያ ለማስፈፀም ፈቃደኛ ያልሆኑ ርዕሳነ-መምህራን በፈቃዳቸው ከሃላፊነታቸው ለመነሳት መልቀቂያ እያስገቡ ነው።

ኢህአዴግ፤ የመንግስት ተቀጣሪ መምህራንን ለማባረር አዲስ ስልት መቀየሱን ውስጥ አዋቂ ምንጮች አጋለጡ፡፡

ቀደም ሲል  መምህራን ፦“የሙያችን ክብር ተነክቷል፣ ዳቦ ለመብላት የሚያስችልና ከሁሉም ሙያዎች ጋር ትይዩ የሆነ የደሞዝ ማስተካከያ ስኬልና  ጭማሪ ይደረግልን” የሚሉ ጥያቄዎችን በማንሳት  ሥራ እስከማቆም መድረሳቸው  የሚታወስ ሲሆን፤ ይህንኑ ተከትሎበአዲስ አበባና በተለያዩ ክልሎች በርካታ መምህራን ከሥራ መባረራቸውን ይታወቃል፡፡

ውስጥ አዋቂ ምንጮች እንደሚሉት ፤ሰሞኑን ደግሞ ኢህአዴግ፦”ተቃዋሚ ናቸው”የሚላቸውን  መምህራን ለማባረር አዲስ ስልት ቀይሷል፡፡

ምንጮጩ እንዳመለከቱት፤ ኢህአዴግ- የመንግስት ተቀጣሪ መምህራንን ለማባረር ያቀደው፤ ከA እስከ D የተዘረዘሩ ደረጃዎችን በመስጠት ነው፡፡

በዚህም መሠረት የኢህአዴግ አባል ሆነው በባለፈው የስራ ማቆም አድማው ያልተሳተፉ መምህራን “A” ፣ የኢህአዴግ አባል ሆነው በስራማቆም አድማው የተሳተፉ “B” ፣ የኢህአዴግ አባል ሳይሆኑ በስራ ማቆም አድማው ያልተሳተፉ “C” እና የኢህአዴግ አባል ሳይሆኑ በአድማው የተሳተፉ መምህራን “D”  እንዲሰጣቸው መሪያው ወርዷል።

ለየርዕሳነ-መምህራን የወረደው ይህ መመሪያ፤ በዚህ ድልድል መሰረት በመጨረሻው ምድብ የተቀመጡት ማለትም  “ዲ” የሚያገኙት  መምህራን ከስራቸው እንዲባረሩ   ያዛል።

“ኢህአዴግን ይቃወማሉ” የሚባሉትን መምህራን   ያባርሩ ዘንድ  ይህ  የሸፍጥ መመሪያ  ከደረሳቸው  ርዕሳነ መምህራን መካከል ጥቂት የማይባሉት በሃሳቡ ባለመስማማታቸው ከኃላፊነታቸው  ለመነሳት መልቀቂያ እያስገቡ መሆናቸውን ውስጥ አዋቂ ምንጮቹ  ለፍኖት ተናግረዋል።

መምህራን የመብት ጥያቄ ማንሳታቸውን ተከትሎ  ኢህአዴግ መራሹ መንግስት ከመምህራን  ጋር እልክ  መጋባቱን  የሚናገሩት እነዚሁ ምንጮች፤“መንግስት ነገሮችን ከማባባስ ይልቅ ለምን  ችግሮችን በውይይት  መፍታት እንደማይመርጥ እንቆቅልሽ ሆኖብናል” ብለዋል።

የግንቦት ሰባት ሊቀ-መንበር ዶክተር ብርሀኑ ነጋ  አልፎ አልፎ በሚሰጧቸው ጋዜጣዊ መግለጫዎች ኢህአዴግን ከአንድ ጥጋበኛ የመንደር ጎረምሳ ጋር  ሲያመሳስሉት ይደመጣሉ።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide