በአፍሪካ ቀንድ የተከሰተውን የዝናብ እጥረት ተከትሎ አስቸኳይ እርዳታ በሚቀጥለው አመትም ያስፈሊጋል ተባለ

(ኢሳት ዜና – ሰኔ 30 2009)
ደቡብ ምስራቅ ኢትዮጵያና ሶማሊያን ጨምሮ በአፍሪካ ቀንድ የሚያስፈልገው አስቸኳይ የምግብ ዋስትና እርዳታ ለቀጣዩም የ2018 አመት ካልቀረበ ከፍተኛ አደጋና ችግር ሊያስከትል እንደሚችል አንድ አለም አቀፍ ተቋም አስጠነቀቀ ።
የረሃብ አደጋን ቀድሞ በማስጠንቀቅ የሚታወቀውና ፊውስኔት የተባለው አለም አቀፍ ተቋም እንዳስጠነቀቀው የዘንድሮው አመት የዝናብ መጠን አጥጋቢ ባለመሆኑ አስቸኳይ የምግብ እርዳታው ለአፍሪካ ቀንድ ሃገራት በሚቀጥለው አመትም ካልቀረበ አደጋው የከፋ ሊሆን ይችላል ።በተለይም በደቡብ ምስራቅ ኢትዮጵያና በሶማሊያ እጅግ የከፋ የምግብ እጥረት ሊከሰት እንደሚችል ተቋሙ አስጠንቅቋል ።
በአለም አቀፍ ተቋሙ መግለጫ መሰረት ከነዚሁ ሃገሮች በተጨማሪም በኬንያ ፣በየመን ፣ በደቡብ ሱዳንና በሌሎችም የአፍሪካ ቀንድ ሃገራት ችግሩ ተባብሶ ሊቀጥል ይችላል ።እንደ ፊውስኔት መግለጫ በአፍሪካ ቀንድ በተለይም በአርብቶ አደር አካባቢዎች የሚላስና የሚቀመስ ምግብ በቀጣዩ የፈረንጆች አመት ማለትም በ2018 ላይም ላይኖር ይችላል ። እናም አስቸኳይ የምግብ ዋስትና እርዳታው ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተቋሙ ጥሪ አቅርቧል ። በተለይ ደግሞ በኢትዮጵያ ቆሬ ዞን እንዲሁም ሙዳግ እና ጋላግዱድ በተባሉ የሶማሊያ ዞኖች የዝናቡ መጠን ከ50 በመቶ በታች ዝቅ በማለቱ ችግሩ የከፋ ሊሆን እንደሚችል ተተንብዩል ።
በኢትዮጵያ ሶማሊ ክልል በዋርዴርና ቆሬ ዞኖች ካለፉት 36 አመታት ወዲህ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የዝናብ መጠኑ አነስተኛ በመሆኑ የከፋ ድርቅ እና ረሃብ ሊከሰት እንደሚችል ተገምቷል ። በኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከ7.7 ሚሊዮን ህዝብ በላይ በከፋ የምግብ እጥረት ውስጥ የሚገኝ በመሆኑ አለም አቀፍ የረድኤት ድርጅቶች እርዳታ እንዲሰጡ ጥር እየቀረበላቸው ይገኛል ።በሃገሪቱ የሚገኘው አገዛዝ ግን አለም አቀፍ እርዳታውን ቢፈልገውም ያለምንም እገዛ ድርቁን መቋቋም እችላለሁ በማለት ተደጋጋሚ መግለጫ ሲሰጥ መቆየቱ ይታወሳል ። ይህም ሆኖ ግን በድርቁ ሳቢያ በተለይም በሶማሌ ክልል በርካታ ህጻናት መሞታቸውን የአለም የምግብ ድርጅትን ጨምሮ አለም አቀፍ የረድኤት ድርጅቶች ሲገልጹ መቆየታቸው አይዘነጋም ።