በአፋር የመንግስት ሰራተኞች ያለፈቃዳቸው ለብሄር ብሄርሰቦች በአል በሚል ግማሽ ደሞዛቸው ተወሰደባቸው

መጋቢት ፳፰ (ሃያ ስምንት)ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የመንግስት ሰራተኞች ለኢሳት እንደገለጹት ለበአሉ በሚል ደሞዛቸው ያለፈቃዳቸው መቆረጡን ካወቁ በሁዋላ፣ አቤቱታ ማሰማታቸውን ተከትሎ በአዋሽ አርባ ዞን የጤና ባለሙያዎችን ማክሰኞ መጋቢት 26 ቀን 2009 ዓም በመስብሰብ ለማወያየት ቢሞክሩም ፣ ሰራተኞች ግን ድርጊቱን በመቃወም አልተቀበሉትም። በዚህ የተበሳጩት ባለስልጣናት እናንተ ፈቃደኞች ሆናችሁም አልሆናችም ደሞዛችሁ ይቆረጣል በማለት የእብሪት መልስ ሰጥተዋል። ዛሬ መጋቢት 28 ደግሞ ከመምህራን ጋር ለመነጋገር ከሰአት በሁዋላ ስብሰባ የጠሩ ቢሆንም፣ መምህራን ድርጊቱን ሲቃወሙ ሰብሳቢዋ “ እናንተ የሌላ በሄር ተወላጆች ስለሆናችሁ ነው አናዋጣም የምትሉት” በማለቷ መምህራን በንዴት አዳራሹን ጥለው ወጥተዋል። መምህራን ከ5 በመቶ በላይ አንሰጥም እሱም ቢሆን ተገደን እንጅ በፈቃዳችን አይደለም ብለዋል።
ለአባይ ግድብ እና ለመሳሰሉት ዝግጅቶች ከሰራተኛው ላይ ደሞዝ በግድ እንደሚቆረጥ በተደጋጋሚ ተዘግቧል።