በአፋርና አማራ ድንበሮች በተነሳ ግጭት ከ 15 በላይ ሰዎች ቆሰሉ

ሚያዝያ ፴ ( ሠላሳ ) ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ባለፈው ሳምንት በአዳር ወረዳ ከባቲ 15 ኪ ሜ ርቀት ላይ በሚገኝ ቦታ ላይ ከድንበር ይገባኛል ጥያቄ ጋር በተያያዘ በተነሳ ግጭት ከ15 በላይ ሰዎች መቁሰላቸውን ምንጮች ገልጸዋል።
ግጭቱ በተቀሰቀሰበት ወቅት በአካባቢው የነበሩ የአጋዚ ወታደሮች ሁኔታውን ለማብረድ ምንም አይነት እንቅስቃሴ አለማሳየታቸው ነዋሪዎችን ግራ አጋብቶአል ።
እንደ ወረዳው ነዋሪዎች ገለጻ በአካባቢው ከዛሬ ነገ ይፈነዳል የሚል ከፍተኛ ውጥረት የነገሰ ሲሆን፣ አብዛኛው ህዝብ ግጭቱ ይሰፋል የሚል ስጋት ውስጥ ወድቋል። ከአንድ ወር በፊት በአካባቢው በሚነሱ ግጭቶች ዙሪያ የሁለቱ ክልል ባለስልጣናት ተገናኝተው ተነጋግረው ነበር።
በቅርቡ በሶማሌና ኦሮምያ ድንበር አካባቢም ከ 200 በላይ ሰዎችን ለሞት የዳረገ ደም አፋሳሽ ግጭት መካሄዱ አይዘነጋም። በሌላ በኩል ወደ ሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ከፍ ያለ ወታደራዊ እንቅስቃሴ እየታየ መሆኑን ከየአካባቢው የሚደርሱን መረጃዎች ያመለክታሉ።
ባለፈው ሳምንት በርካታ ታንኮች ተገዝተው ወደ አገር ውስጥ መግባታቸውን ተከትሎ ቅዳሜ ዕለት ወታደሮችን የጫኑ በርካታ አውቶቡሶች በደብረብረሃን በኩል አድርገው ወደ ሰሜንተጉዘዋል።