በአዳማ ከተማ ሙሉ ለሙሉ መብራት በመቋረጡ ነዋሪዎቹ ተቸግረናል እያሉ ነው

ሰኔ ፲፮( አሥራ ስድስት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ፋብሪካዎች ተዘግተዋል በአዳማ ከተማ ከሃሙስ ሰኔ 16 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ ሁለት ቀናት የመብራት አገልግሎት መቁረጡን ተከትሎ ከተማዋ ሙሉ ለሙሉ በጨለማ መዋጧን ምንጮቻችን አስታውቀዋል።
ከመብራት መቋረጥ ጋር በተያያዘ ፋብሪካዎች፣ የሕክምና መስጫ ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶች እና የተለያዩ ማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ስራቸውን ለማቆም ተገደዋል።
በተጨማሪም በተወሰኑ የከተማ ክፍል የስልክ እና የውሃ አገልግሎት በመቋረጡ ነዋሪዎቹ መቸገራቸውን አስታውቀዋል። የመጠጥ ውሃ በጀሪካን ከሩቅ ለመግዛት በመገደዳቸው ለተጨማሪ ወጭዎች መጋለጣቸውን ነዋሪዎቹ በምሬት ይናገራሉ።
በተለይ በቤት እንስሳት እርባታ ላይ ለተሰማሩ ባለሃብቶች መስተዳድሩ የውሃ እደላ ለማድረግ እንኳን ፈቃደኛ ለመሆኑ እንዳሳዘናቸው ባለሃብቱ ቅሬታ ፈጥሮባቸዋል።
”አስቀድሞ መሰረተ ልማቶች በበቂ ሁኔታ ሳይዘረጉ በአፋጣኝ ፋብሪካዎችን እንድንከፍት መደረጋችን አግባብ አልነበረም።
በተደጋጋሚ ጊዜያት መብራት ስለሚጠፋ ለከፍተኛ ኪሳራ ተዳርገናል። ” በማለት አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የግል ባለሃብት ምሬታቸውን ገልጸዋል።
ከተማዋ ከጊዜ ወደ ጊዜ ከፍተኛ የሕዝብ ብዛት እያስተናገደች የመጣች ቢሆንም ተመጣጣኝ የሆነ የመሰረተ ልማት ተጠቃሚ ለመሆን ግን አልታደለችም።
የአዳማ ከተማ መስተዳድር በበኩሉ የነዋሪዎችን ችግሮች አድምጦ አፋጣኝ ምላሽ መስጠት ተስኖታል። በተመሳሳይም በደብረማርቆስ ከተማ የመብራት አገልግሎት በመቋረጡ ነዋሪዎቹ ለከፍተኛ ችግሮ መዳረጋቸውንም ምንጮች አክለው ገልጸዋል።