በአዲግራት ዩኒቨርስቲ አንድ ተማሪ ህይወቱ አልፎ ተገኘ

ጥር ፳፪ (ሃያ ሁለት)ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የኢሳት ምንጮች እንደገለጹት የአዲግራት ዩኒቨርስቲ 1ኛ አመት ተማሪ የነበረው ሹሚ ለማ በቀለ ጥር 15 ቀን 2009 ዓም ተገድሎ አስከሬኑ ለቤተሰቦቹ ከተላከ በሁዋላ ጥር 19 ቀን 2009 ዓም ተክለሃይማኖት ቤተክርስቲያን ተቀብሯል።
የሰንዳፋ ድሬ አካባቢ ተወላጅ የሆነው ተማሪ ሹሜ ጥር 15 ቀን ፈተና እንደጨረሰ ለወላጆቹ ስልክ ደውሎ በሁለት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ እንደሚመለስ ተናግሮ ነበር። ጥር 16 በቤተመጽሃፍት ውስጥ ሲያጠና መታየቱን፣ ይሁን እንጅ ምሽቱን ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ ዶርሙ ውስጥ ተገድሎ መገኘቱንም ምንጮች ገልጸዋል። አስከሬኑ በዩኒቨርስቲው መኪና እና በፖሊስ ታጅቦ ለወላጆቹ የተሰጠ ሲሆን፣ የሟች አክስት ከወላጆቹ ጋር በመሆን አስከሬኑን አሳዩን ቢሉም ፖሊሶች ፈቃደኛ አልሆኑም። የአስከሬን ምርመራ እንዳይደረግም ፖሊሶች የአስከሬን ጥበቃ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ምንጮች ገልጸዋል።
አስከሬን አይተናል የሚሉ ወገኖች ተማሪው መገደሉን ይገልጻሉ። በአዲግራት ዩኒቨርስቲ በቅርቡ ተቃውሞ ተነስቶ እንደነበር መዘገባችን ይታወሳል። በጉዳዩ ዙሪያ የዩኒቨርስቲውን ባለስልጣናት ለማነጋገር ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም።