በአዲስ አበባ የነዳጅ ማደያዎችን ለማቃጠል ተንቀሳቅሰዋል የተባሉ የሽብር ክስ እንደተመሰረተባቸው ተገለጸ

ኢሳት (መጋቢት 15 ፥ 2009)

በአዲስ ከተማ በሚገኙ ከሰባት በላይ የነዳጅ ማደያዎችን ለማቃጠል ተንቀሳቅሰዋል የተባሉ ዘጠኝ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው የሽብርተኛ ክስ እንደተመሰረተባቸው ጠቅላይ አቃቤ ህግ አርብ ገለጸ።

ድርጊቱን ለመፈጸም ሲንቀሳቀሱ ነበር የተባሉ ተጠርጣሪዎች በውጭ ከሚገኝ የሽብር ድርጅት በተለያዩ ማህበራዊ መገናኛዎች ተልዕኮ ሲቀበሉ ነበር ሲል ከሳሽ አቃቤ ህግ በክሱ ማመልከቱን የሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል። ይሁንና ጠቅላይ አቃቤ ህግ ተጠርጣሪዎቹ ተልዕኮ ሲቀበሉ ነበር ያለውን ድርጅት በስም አልጠቀሰውም።

ከዘጠኙ ተጠርጣሪዎች መካከል ሶስቱን ብቻ በስም የጠቀሰው ጠቅላይ አቃቤ ህግ ግለሰቦቹ በአዲስ አበባ መካኒሳ ጀርመን አደባባይ፣ ጭላሎ ሆቴል አካባቢ፣ ቦሌ ኤርፖርት እንዲሁም ቃሊቲ እና አየር ጤና አካባቢዎች የሚገኙ የነዳጅ ማደያዎችን ለማቃጠል እንደተንቀሳቀሱ በራሱ አቅርቧል።

አንደኛ ተከሳሽ ክንፉ መሃመድ በውጭ ሃገር ከሚገኙት የሽብር ቡድን አመራሮች ጋር በማዕከላዊ መገናኛዎች ተልዕኮን ሲቀበል እና ሌሎች አባላትን እንደመለመለ አርብ በቀረበው ክስ ተመልክቷል።

ተጠርጣሪዎች ወደ ተለያዩ ማደያዎች በማምራት የጥበቃውን ሁኔታ እና ቃጠሎውን ለመፈጸም አመቺውን ጊዜ ሲያጤኑ ቆይቷል ያለው ከሳሽ ጠቅላይ አቃቤ ህግ መስከርም 26, 2009 አም ሌሊት ስምንት ሰዓት ቃጠሎውን ለመፈጸም እቅድ ተይዞ ነበር ሲልም ለፍርድ ቤት አቅርቧል።

ይሁንና በዕለቱ ተጠርጣሪዎቹ የአካባቢው ሁኔታ ድርጊቱን ለመፈጸም ስላላቻላቸው መመለሳቸውንና ቃጠሎው ሳይካሄድ መቅረቱን አቃቤ ህግ በራሱ ዘርዝሯል።

ተጠርጣሪዎቹ ድርጊቱን ባይፈጽሙም፣ ለመፈጸም ያቀዱ፣ የተዘጋጁ ያሴሩ፣ ያነቡና የሞከሩ በሚል የሽብርተኝነት ክስ መስርቶባቸዋል።

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ክሱን በችሎት ለማንበብ ለመጋቢት 21 ቀን 2009 አም ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱም ታውቋል።