በአዲስ አበባ የሚገኙ አብያተ-ክርስቲያናት ለአባይ ግድብ እያንዳንዳቸው 50ሺህ ብር፣ ካህናትም የአንድ ወር ደሞዛቸው እንዲያዋጡ በድጋሚ ታዘዙ

ኢሳት ( መጋቢት 27 ፥ 2009)

ለአባይ ግድብ ግንባታ በአዲስ አበባ የሚገኙ አብያተ-ክርስቲያናት እያንዳንዳቸው 50ሺህ ብር እንዲያዋጡ በድጋሚ ታዘዙ። በአብያተ-ክርስቲያናቱ የሚያገለግሉ ካህናትም የአንድ ወር ደሞዛቸውን ለግድቡ ግንባታ እንዲሰጡ ተወስኗል።

በጠቅላይ ቤተክህነት የሚገኙ የእሳት ምንጮች እንደገለጹት በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ 90 ያህል አብያተ-ክርስቲያናት እያንዳንዳቸው የሚያዋጡት 50ሺህ ብር እንዲሁም የካህናቱ የአንድ ወር ደሞዝ በጠቅላይ ቤተ-ክህነት በኩል ለህዳሴው ግድብ ብሄራዊ ምክር ቤት ገቢ እንዲያደርጉ ተወስኗል።

በ5 አመት ይጠናቀቃል በሚል ከ6 አመት በፊት ግንባታው የተጀመረው የህዳሴው ግድብ ህጻናት ጭምር በትምህርት ቤት መዋጮ የተጠየቁበት ሲሆን፣ እስካለፈው ሳምንት ከህዝብ የተሰበሰበው ገንዘብ 9.6 ቢሊዮን ብር እንደሆነም ተመልክቷል። ቃል የተገባው ገንዘብ 12.6 ቢሊዮን ብር ቢሊዮን ብር እንደነበርም ብሄርዊ ምክር ቤቱ አስታውቋል።

ወደ አንድ መቶ ቢሊዮን ብር የሚጠይቀው የህዳሴ ግድብ በአሁኑ ወቅት 57 በመቶ መድረሱንም የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።