በአዲስ አበባ ከተማ ከንግድ ይዞታቸው የተፈናቀሉ ነጋዴዎች ለከፍተኛ ስቃይ ተዳረጉ

ጥር ፩ (አንድ)ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- በልማት ስም በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ለዘመናት ሃብት አፍርተው በንግድ ስራ ላይ ይተዳደሩበት ከነበሩት ይዞታቸው የተፈናቀሉ ነጋዴዎች ለሶስት ዓመታት በስቃይ ላይ መሆናቸውን አስታወቁ።

ነጋዴዎቹ ቤተሰባቸውን ከሚያስተዳድሩበት ይዞታቸው ተነስተው በምትኩ ተለዋጭ ቦታ ይሰጣችኋል ቢባሉም እስካሁን ድረስ መስተዳድሩ የገባላቸውን ቃል አላከበረም። ቁጥራቸው ከአንድ ሺሕ በላይ የሚሆኑት እነዚህ ነጋዴዎች ከአስር በላይ የአክሲዮን ማኅበራትን መስረተው ተደራጅተው ጉዳያቸውን ቢከታተሉም ሰሚ አካል አላገኙም።

በልደታ ክፍለ ከተማ ሦስት፣ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ስምንት፣ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ሦስት የአክሲዮን ማኅበራት አቤቱታ ቢያቀርቡም ጉዳያቸውን አስመልክቶ ምላሽ የሰጣቸው አካል የለም። ከ1996 ዓ.ም ጀምሮ በልደታ ክፍለ ከተማ ተክለሃይማኖት አካባቢ የነበረው 33 ሄክታር የንግድ ይዞታቸውን ያጡት 122 ነጋዴዎቹ 24 ሚሊዮን ብር በማዋጣት በባንክ አስቀምጠው ‹‹ጥቁር አንበሳ አክሲዮን ማኅበር›› በሚባል ስያሜ የንግድ ድርጅት ያቋቋሙ ቢሆንም በምትኩ የተሰጣቸው ነገር የለም።

በሊዝ አዋጁ ከመልሶ ማልማት ቦታዎች የሚነሱ ነጋዴዎች በተለይም የቀበሌ ወይም የመንግሥት የንግድ ቤት ተከራዮች፣ በአማካይ በነፍስ ወከፍ 25 ካሬ ሜትር እንዲሰጣቸው በሕግ የተፈቀደ ቢሆንም በመሰተዳድሩ ውስብስብ አሰራር ምክንያት ለስቃይ ተዳርገዋል። በተጨማሪም ከዋቢ ሸበሌ ሆቴል ጀርባ በሚገኘው 10.6 ሄክታር ይዞታቸው በመልሶ ማልማት ፕሮግራም ስም የተፈናቀሉ 124 ነጋዴዎች 19 ሚሊዮን ብር አዋጥተው ‹‹ተደንጓ የመልሶ ማልማት አክሲዮን ማኅበር›› አቋቁመው ተለዋጭ ቦታ እንዲሰጣቸው ቢጠባበቁም ምላሽ ተነፍጓቸዋል።

ከነባር ይዞታቸው የተፈናቀሉት ነጋዴዎች ተለዋጭ የንግድ ቦታ ይዞታ አለመሰጠቱ በራሳቸው እና በቤተሰባቸው ሕይወት ላይ ከፍተኛ የሆነ ጫና መፍጠሩን  ሪፖርተር ያነጋገራቸው የማኅበሩ ከፍተኛ አመራሮች ገልፀዋል።