በአዲስ አበባ ኤች አይ ቪ ኤድስ በከፍተኛ መጠን እየተስፋፋ ነው ተባለ

ኢሳት (ሰኔ 2 ፥ 2009)

በአዲስ አበባ ከተማ የኤች አይ ቪ ኤድስ ስርጭት በከፍተኛ መጠን እየጨመረ መምጣቱንና የበሽታው ስርጭት በዚሁ ከቀጠለ ወረርሽኝ ድረጃ ሊደርስ እንደሚችል ተገለጸ።

በከተማዋ በርካታ መዝናኛዎች መስፋፋታቸው እና ጥንቃቄ የጎደለው የግብረ ስጋ ግንኙነት ለበሽታው ስርጭት ዋነኛ ምክንያት መሆኑን የአዲስ አበባ ጤና ቢሮን ዋቢ በማድረግ የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

የበሽታው ስርጭት እየጨመረ መምጣትን ተከትሎ በአዳማ ከተማ ሃገር አቀፍ ምክክር በመካሄድ ላይ ሲሆን፣ ጋምቤላና ሶማሌ ክልልም የባይረሱ ስርጭት በከፍተኛ ድረጃ እየጨመረ መሆኑ ተመልክቷል።

አዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ በተለያዩ የሃገሪቱ ክልሎች የኤች አይ ቪ ባይረስ ስርጭት በከፍተኛ መጠን ቀንሷል ተብሎ ለረጅም ጊዜ ሲገለፅ መቆየቱ ይታወሳል።

ይሁንና በሽታው በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ በከፍተኛ መጠን ዳግም በመሰራጨት ላይ ሲሆን፣ ስርጭቱ በዚሁ የሚቀጥል ከሆነ ወረርሽን ደረጃ ሊደርስ እንደሚችልም በመድረኩ ተገልጿል።

የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ዶ/ር ወርቁ ከበደ ችግሩን ለመቅረፍ ህብረተሰቡ የህክምና አገልግሎትና ምክር የሚያገኝበት ሁኔታ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስቧል።

የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በሽታው ዳግም አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን ቢገልፅም የስርጭቱ መጠን ምን ደረጃ እንደደረሰና በበሽታው የተያዙ ሰዎችን ቁጥር ከመግለጽ ተቆጥቧል።

እስከቅርብ ጊዜ ድረስ በኢትዮጵያ ከሁለት ሚሊዮን በላይ የሚደርሱ ሰዎች ከቫይረሱ ጋር እንደሚኖሩ ሲገልፅ ቆይቷል።

እስከ ቅርብ አመታት ድረስ የበሽታ ስርጭቱ መጠን 2.4 በመቶ እንደነበርና በየአመቱ በ 0.29 በመቶ ይጨምር እንደነበር UNAIDS (የተባበሩት መንግስታት ድርጅት) መረጃ ያመለክታል።

ኢትዮጵያ የ HIV/AIDS ስርጭትና ሞት ከሚመዘገብባቸው የአፍሪካ ሃገራት ግንባር ቀደም መሆኗ ሲገለፅ ቆይቷል።