በአዲስ አበባ ተግባራዊ ይሆናል ተብሎ የሚጠበቀው የቀን ገቢ ግምት አሰራር አድሎአዊ እንደነበረ ተገለጸ

ኢሳት (ሰኔ 13 ፥ 2009)

የአዲስ አበባ አስተዳደር የገቢዎች ኤጀንሲ በግንቦት 30 ቀን 2009 አ ም እንዳጠናቀቀ ይፋ ያደረገው የቀን ገቢ ግምት የስነ-ምግባር ችግር ያለበት በሙስና በዘመድ አዝማድና የፖለቲካ አባልነት ምክንያት አድሎአዊ አሠራር የተከተለ መሆኑን የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ገለጹ።

ይህ የተገለጸው የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባላስልጣና የአዲስ አበባ ከተማ ታክስ ፕሮግራም ዘርፍ በቀን ገቢ መረጃ አሰባሰብ ሂደት ላይ ከነጋዴ ተወካዮችና የነዋሪዎች ፎረም ጋር በኔክሰስ ሆቴል በተደርገው ስብሰባ ላይ ነው።

ስብሰባውን የመሩት የአዲስ አበባ አገር ውስጥ ታክስ ፕሮግራሞች ዘርፉ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ነጻነት አበራ የቀን ገቢ ግምቱ በግንቦት 30 ቀን 2009 አም መጠናቀቁን የገለጹ ሲሆን የተገኘውን ውጤት ተከትሎ የግብር ከፋዮች የደረጃ ለውጦችና ማሻሻያዎች እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል። ምክትል ዋና ዴሬክተሩ አያይዘውም የቀን ገቢ ግምት የተሰራላቸው ነጋዴዎች ለእያንዳንዳቸው ምን ያህል አንደሚከፍሉ በደብዳቤ የሚላክ መሆኑን ገልጸዋል።

ወይዘሮ ነጻነት አበራ ባቀረቡት ሪፖርት በሚያዚያና ግንቦት ወር ብቻ የ147 ሺህ 473 ነጋዴዎች የቀን ገቢ ሽያጭ ግምት የተሰራላቸው መሆኑን ቢገልጽም በስብሰባው የተገኙት ነጋዴዎች አሰራሩ ላይ ከፍተኛ ቅሬታ አቅርበዋል።

ነጋዴዎች ካቀረቧቸው ተቃውሞዎች መካከል የቀን ገቢ ግምት የሚሰሩት “ገማች ኮሚቴ” አባላት የወረዳ ካድሬዎች፣ በነዋሪ ፎረም ስም የተደራሹ የፎረም እና የኢሀዲግ አባላት አንዲሁም በጉቦና ሙስና የሚሰሩ የገቢዎችና ጉምሩክ ሰራተኞች በመሆኑ ኢፍትሀዊ አንደሆነ ተናግረዋል። “የገማች ኮሚቴ’’ አባላት ከአንዳንድ ነጋዴዎች ጋር በሚፈጥሩት ትስስር ነጋዴዎች እቃቸውን ከሱቅ መደብራቸው አስቀድመው እንዲያሸሹ መረጃ በመስጠት የቀን ገቢ ግምታቸውን በቅጽ ላይ ሲውሉ አሳንሰው በመመዝገብ ግምት በሚካሄድበት ቀን ነጋዴዎች ሱቃቸውን ዘግተው እንዲጠፉ አስቀድሞ መረጃ በማቀበል እንደሚሰሩ ገልጸዋል። ከዚህ በተጨማሪም ታላላቅ ባለስልጣናት በኮንትሮባንድ እና ህገ-ውጥ ንግድ ጀርባ የተሰማሩ በመሆኑ የንግድ አንቅስቃሴው ላይ ፍትሃዊነት እንዲጎድለው ማድረጋቸውን ገልጸዋል።