በአዲስ አበባ ቆሻሻ መድፊያ ቦታ በደረሰው አደጋ የሟቾች ቁጥር እያሻቀበ ነው።

መጋቢት ፭ (አምስት)ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በአዲስ አበባ በተለምዶ ቆሸ ሰፈር እየተባለ በሚጠራው አካባቢ በደረሰው አደጋ ሟቾች ቁጥር ከ90 በላይ የደረሰ ሲሆን፣ አሁንም በርካታ ዜጎች ከተቀበሩበት አፈር አልወጡም። ዛሬ ማክሰኞ ከ40ያላነሱ ሰዎች ተገኝተዋል። ከተገኙት አስከሬኖች መካከል ከወለደች 3 ወሩዋ የሆነችው አራስ እና የልጇ እንዲሁም ሁለት ቁራን በመቅራት ላይ የነበሩ ታዳጊዎች ይገኝበታል። ወላጆችም ዛሬም አካባቢውን ከበው ሲያለቅሱ ውለዋል። በጭንቀት ውስጥ የሚገኙት ወላጆች፣ ተስፋ በመቁረጥ አስከሬን ከሚቆፍሩ ወጣቶች ጋር ተጋጭተዋል። የአዲስ አበባ መስተዳድር አፋጣኝ እርዳታ ባለማድረጉም እየወቀሱ ነው።
ካሌብ ጸጋየ የተባለ አንድ ግለሰብ “ ማንም እየረዳን አይደለም፣ ቁፋሮውን የምናካሂደው እራሳችንን ነን። ያሳፍራል” ሲል ለአልጀዚራ ተናግሯል። አንዳንዶች ቁፋሮውን በእጃቸው ሲያካሂዱም ይታያል።
“ልጆቼ ልጆቼ” እያለሁ የሚያለቅሱ አንድ አባት፣ 4 ልጆቻቸውንና ባለቤታቸውን ማጣታቸውን አልጀዚራ ዘግቧል። አንድ ከእናቱ ላይ የተናኝ ህጻን ጨምሮ 3 አስከሬን በተገኘበት ወቅት ፣ የአካባቢው ህዝቡ ለቅሶውን አሰምቷል።
የመገናኛ ብዙሃን ስፍራው ሲደርሱ አንዳንዶች መስተዳድሩን ማውገዛቸውን የገለጸው አልጀዚራ፣ ሁለት ስካቫተሮችና 3 አምቡላንሶች ብቻ በአዲስ አበባ መስተዳደር መመደባቸውን ዘግቧል። ጋዜጠኞች ካሜራቸውን ይዘው ወደ ስፍራው ሲጠጉ፣ ነዋሪዎች ፣ “ አቁሙ አታስመስሉ፣ ምንም ድጋፍ አላደረጉልንም፣ የእጅ ጓንት እንኳን አልሰጡንም፣ በማታ እንኳን ሞባይላችንን እያበራን ነው ፍለጋ የምናካሂደው” ሲሉ በቁጣ ተናግረዋል።
ባለስልጣኖቹን ለ10 አመታት ስናስጠነቅቅ ነበር ያሉት የ48 አመቱ አቶ ታየ ወለደአማኑኤል፣ በአገዛዙ በኩል ምንም መልስ ሳይሰጣቸው መቆየቱን ተናግረዋል።
አምነስቲ ኢንተርናሽናል በደረሰው አደጋ መንግስት ሙሉ በሙሉ ተጠያቂ መሆኑን ገልጿል። መንግስት የቆሻሻ መሙያው መሙላቱን እያወቀ ይጠቀምበት ነበር። በአካባቢው የሚኖሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች እንዲኖሩበት ፈቀደ ያሉት፣ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የምስራቅ አፍሪካ ዳይሬክተር፣ ሚ/ር ሙቶኑ ዋኒየኪ፣ እነዚህ ሴቶችና ህጻናት በዚህ አደገኛ ቦታ እንዲኖሩ የተገደዱት መንግስት ለዜጎቹ በቂ ቤትና ተገቢውን ስራ ባለማቅረቡ ነው” ሲሉ አክለዋል።
መንግስት የጠፉ ዜጎችን አፈላልጎ እንዲያሳውቅ እንዲሁም ለተረፉት አማራጭ ቤት እንዲያዘጋጅላቸው ሙቶኒ ጠይቀዋል። ተገቢው ምርመራ ተካሂዶ የአደጋው መንስኤ እንዲታወቅና ተጠያቂ የሚሆኑ ባለስልጣናትም እንዲጠየቁ አምነስቲ ጠይቋል።
በአካባቢው ያሉ ነዋሪዎች ለኢሳት እንደገለጹት ከሆነ ደግሞ፣ አገዛዙ ወታደሮችን ሁሉ አሰማርቶ ተቃውሞ ሊነሳ ይችላል በሚል ቁጥጥር እያደረገ ነው። ይህም በአካባቢው ውጥረት እንዲሰፍን አድርጓል።