በአዲስ አበባ ቆሻሻ መድፊያ ቦታ ላይ የደረሰውን አሰቃቂ አደጋ ተከትሎ የተሰበሰበው ገንዘብ እስካሁን አለመከፋፈሉ በተፈናቃዮች ዘንድ ከፍተኛ ቅሬታ አስነስቷል።

ግንቦት ፯ ( አባት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በተለምዶ ቆሼ እየተባለ በሚጠራው የቆሻሻ መድፊያ ላይ በደረሰው ናዳ በርካታ ሰዎች መሞታቸውንና መፈናቀላቸውን ተከትሎ፣ ኢትዮጵያውያን የእርዳታ እጃቸውን በመዘርጋት በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ለተጎጂዎች ቢሰጡም፣ የባንክ ሂሳቡን የሚቆጣጠረው ገዢው ፓርቲ ገንዘቡን ለተጎጂዎች ባለማከፋፈሉ ማዘናቸውን የተጎጂ ቤተሰቦች ተናግረዋል።
በቅርቡ የመስተዳድሩ ባለስልጣናት ለተጎጂዎች የሚሰጣቸውን የኮንዶሚኒየም ቤት እና ቦታ ቢያስታወቁም፣ እስካሁን ድረስ ቃል የገቡትን ቤትና ቦታ ማስረከብ ባለመቻላቸው ብዙዎች ከሰዎች ቤት ተጠግተው ህይወታቸውን እንዲገፉ አድርጓቸዋል። ከሁሉም በላይ የተሰበሰበውን በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ በጊዜው ለመስጠት ባለመቻሉ፣ ለከፍተኛ ችግር መዳረጋቸውን ነዋሪዎች ገልጸዋል።
እያንዳንዷን ቀን በችግር ነው የምናሳልፈው የሚሉት ነዋሪዎች፣ ኢትዮጵያውያኖች በፍጥነት ለችግራችን ሲደርሱልን፣ ገንዘቡን የተቀበለው መንግስት ግን የሰበሰበውን ገንዘብ ለማከፋፈል እያመነታ ነው ሲሉ ተናግረዋል።