በአዲስ አበባ ስታዲየም ለድብድብ የተገባበዙትን ባለሥልጣናት ፤ የዕለቱ የክብር እንግዳ ተነስተው ገላገሉ

ሰኔ ፮ (ስድስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ነገሩ የሆነው፤በብራዚል ለሚደረገው የአለም ዋንጫ ማጣሪያ ኢትዮጵያና -የመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ ባለፈው እሁድ  በአዲስ አበባ ስታዲዮም  ግጥሚያ ሲያደርጉ ነው።

ጠቡ የተፈጠረውም፤ ጨዋታውን ለመመልከት በክቡር ትሪቡን በታደሙ ሁለት  ባለሥልጣናት መካከል ነው-በደደቢት ስፖርት ክለብ መስራች እና ፕሬዚዳንት  በኮሎኔል አወል ኢብራሂም እና በስፖርት ኮሚሽነሩ በ አቶ አብዲሳ ያደታ መካከል።

የሁለቱም ባለስልጣናት  ጠባቂዎች ጠቡን ለማብረድ ያደረጉት ሙከራ በባለስልጣናቱ እምቢተኝነት ሊሳካ ሳይችል ቀርቶ ወደ ቦክስ ሲያመሩ  የዕለቱ ዋነኛ  የክብር እንግዳ የሆኑት የውሀ እና ማዕድን ሚኒስትሩ አቶ አለማየሁ ተገኑ ከመቀመጫቸው በመነሳትና በመገላገል ጸቡን ማብረዳቸውን የፍኖት ዘገባ ያመለክታል።

የጠቡ መንስዔም ጨዋታው በሚካሄድበት ጊዜ ከስፖርት ኮሚሽነሩ ጎን የተቀመጡት የደደቢቱ ኮሎኔል አወል በስሜት ተውጠው፦”ያዘው!ሩጥ! አቀብል!…”እያሉ በጩኸት ድጋፋቸውን መግለፃቸው ነው።

በኮሎኔል አወል ሁኔታ የተበሳጩት የስፖርት ኮሚሽነሩም፦”እባክህ ጆሮዬን አሞኛል፤አትጩህብኝ” በማለት ይጠይቃሉ።

የዐይን እማኞች እንዳሉት የደደቢቱ ኰሎኔል አወልም፦‹‹ጆሮህን ካመመህ እዚህ ምን አስቀመጠህ? ሄደህ አትተኛም!›› በማለት የስፖርት ኮሚሽነሩን በመናገራቸው ጠቡ ተጀመረ።

በስፍራው የነበሩት እነዚሁ እማኞች ስለ ዕለቱ ግጭትም ሲያብራሩም፦ ‹‹አለመግባቱ ተካሮ ሁለቱም ለድብድብ ሲነሱ የባለሥልጣናቱ

አጃቢዎችና በሥፍራው ለጥበቃ የተመደቡ ፖሊሶች ፀቡን ለማብረድ  ቢሞክሩም ሊሳካላቸው  ባለመቻሉ የዕለቱ የክብር እንግዳ አቶ አለማየሁ ተገኑ ተነስተው ገላጋይ በመሆናቸው ፀቡ ሊበርድ ችሎአል” ብለዋል።

የፍኖትን ዜና ያነበቡ አንድ አስተያዬት ሰጪ ፦”ኢህአዴግ 99 ነጥብ 6 በመቶ የፓርላማ ወንበር ጠራርጎ በያዘበት የባለፈው ምርጫ ወቅት በደቡብ ክልል በሚገኝ አንድ የምርጫ ጣቢያ ሁለት የመድረክ ተወካዮች እንደተደባደቡ  በተደጋጋሚ ሲነግረን የነበረው ኢቲቪ  የእነዚህን ባለስልጣናት ጠብ ያልነገረን፤  እነሱ ሲጣሉ የሳልሀዲንን ጎሎች እየቀረፀ  ስለነበር ይሆንን?”በማለት ተሳልቀዋል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide