በአወዛጋቢ ሁኔታ የተገደለው የኢትዮጵያ የቡና ደጋፊ ዘነበ በላይ የቀብር ስነስርዓት ተፈጸመ

ሚያዝያ ፳፯ ( ሃያ ሰባት ) ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ከወር በፊት ሲዳማ ቡና ከኢትዮጵያ ቡና የሚያደርጉትን የእግር ኳስ ጫወታ ለመከታተል ወደ አዋሳ ያቀናው የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊ ዘነበ በላይ ከጫወታው በኋላ አድራሻው ጠፍቷል። የዘነበ በላይን አድራሻ ለማግኘት የቡና ደጋፊዎች እና ቤተሰቦቹ የተለያዩ ጥረቶችን ቢያደረጉም ጥረታቸው ሳይሰምር ቀርቷል። እስካሁንም አሟሟቱን አስመልክቶ ግልጽ የሆነ የሚታወቅ ነገር ማግኘት አልተቻለም።
ግድያው በማን እንደተፈጸመ የሚታወቅ ነገር አለመሆኑና አስከሬኑ ሳይመረመር የቀብር ስነስርዓቱ እንዲፈጸም መደረጉ ደጋፊዎችን እና ቤተሰቦቹን አሳዝኗል። አዋሳ ውስጥ በአወዛጋቢ ሁኔታ የተቀበረው አስከሬን ወጥቶ በቡድኑ ደጋፊዎች ጥረት በትውልድ ከተማው አዲስ አበባ እንዲቀበር ተደርጓል።
አራት ኪሎ የተወለደው ዘነበ በላይ ላለፉት 21 ዓመታት ኢትዮጵያ ቡናን ሕይወቱ እስካለፈችበት ቀን ድረስ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል ሲደግፍ የነበረ አመለ ሸጋ ደጋፊ መሆኑን ጓደኞቹ እማኝነታቸውን ሰጥተዋል። ባላደገ እግር ኳስ ላይ የሰው ሕይወት መክፈል አሳዛኝ መሆኑን እና ዘነበ በላይ የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ መስዋእት ነው ሲሉ ደጋፊዎች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
የዘነበ በላይ የቀብር ስነርዓት የኢትዮጵያ ቡና እና የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች እንዲሁም ስፖርት ወዳዶች በተገኙበት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በቀጨኔ መድሀኔዓለም ከቀኑ 10፡00 ላይ ተፈጽሟል።