በአወልያ የሚገኙ ሙስሊሞች ተቋውሞአችንን በመላው መስጊዶች ማሸጋገር እንችላለን ሲሉ አስጠነቀቁ

የካቲት 3 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በአወልያ የሚገኙ ሙስሊሞች ለሰላም ስንል እንጅ፣ ተቃውሞዋችንን በአንዋር መስጊድ እና በመላው አገሪቱ በሚገኙ መስጊዶች ማሸጋገር እንችላለን ሲሉ አስጠነቀቁ

በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሙስሊሞች የአርብ ስግደትን ለማካሄድ በአወልያ በተገኙበት ሰአት እንደተናገሩት መንግስት ለጥያቄቸው መልስ የማይሰጥ ከሆነ ተቃውሞውን በመላ አገሪቱ በሚገኙ መሲኪዶች ሁሉ እንደሚያሸጋግሩት  አስጠንቅቀዋል።

ችግሩን ከመንግስት ባለስልጣናት ጋር ተደራድረው መፍትሄ እንዲፈልጉ ከተወከሉት መካከል አንዱ የሆኑት አቡበክር አህመድ ባሰሙት ንግግር ” ለመንግስት ያቀረቡት ጥያቄ የመብት ጥያቄ በመሆኑ፣ አፋጣኝ  መልስ ሊሰጥ” ይገባዋል።

ሙስሊሙን የማይወክሉት የእስልምና ጉዳዮች ጽህፈት ቤት አመራሮች ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሙስሊሙ ተወካዮች ላይ እርምጃ እንዲወስድ ጥያቄ ማቅረባቸውን፣ ሙስሊሙ የኮሚቴው አባላት የሚያቀርቡትን ጥያቄ እንዳይቀበልና እንዳይተባበር የሚያሳስብ ወረቀት መበተኑን በተለያዩ መንገዶች አመራሩን ለማስፈራራት ሙከራ እየተደረገ መሆኑን ገልጠዋል።

አቶ አቡበክር አያይዘውም መንግስት ከሙስሊሙ ተወካዮች ጋር ውይይት ለማድረግ የሰጠው ረጅም የጊዜ ቀጠሮ ” ሰላማዊ ትግሉን ለመቀልበስ እየተጠቀሙበት ነው” ብለዋል።

የሙስሊሙ ተወካዮች የፊታችን ሰኞ ከመንግስት ባለስልጣናት ለመገናኘት ቀጠሮ ይዘዋል።

መንግስት ለጥያቄያቸው አወንታዊ መልስ ሰጥቶ የእስልምና ምክር ቤት በአዲስ የሚዋቀር ከሆነ፣ ምክር ቤቱ በኤን ጂ ኦ ስም ተመዝግቦ መንግስት በፈለገው ጊዜ የሚዘጋውና የሚከፍተው መሆኑ ከቀረ ፣ የአህባሽ አስተምህሮ መርሀግብር እንዲቋረጥ የሚደረግ ከሆነ እና ሙስሊሞች ሀይማኖታዊ ነጻነታቸውን ያለመንግስት ጣልቃ ገብነት የሚያከናውኑ ከሆነ፣ ትልቅ የነጻነት ድል ተደርጎ ሊቆጠር ይችላል በማለት ጉዳዩን የሚከታተሉ አንድ የሀይማኖት ጋዜጣ አዘጋጅ ገልጠዋል።

መንግስት ለጥያቄው አወንታዊ መልስ ከሰጠ፣ ሌሎች ወገኖችም ተመሳሳይ የመብት ጥያቄዎችን በመያዝ በሰላማዊ ተቃውሞ ድምጻቸውን ማሰማት እንደሚችሉ አክለዋል።

አወልያ ከምርጫ 97 ወዲህ የተፈጠረ ልዩ ክስተት ነው፣ የሌሎች ሀይማኖታዊ፣ ፖለቲካዊ እና ሰብአዊ ድርጅቶች ተመሳሳይ ጥያቄዎችን ለማቅረብ ከአወልያ ልምድ መቅሰም አለባቸው ሲሉ ግለሰቡ ያክላሉ።

በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ሁሉም የእምነት ተቋማት በመንግስት ባለስልጣናት እንደሚሽከረከሩ፣ ተቋማቱ ነጻነት እንደሌላቸው ና በራሳቸው መወሰን እንደማይችሉ አዘጋጁ አክለው አስረድተዋል።

መንግስት በቅርቡ 8 የአልቃይዳ አባላትን ያዝኩ በማለት በመገናኛ ብዙህን ያስተላለፈው ዘገባ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ለመምታት የተጠቀመበት ስልት ሊሆን እንደሚችል አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ።