በአንጎላ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ተካሄደ

(ኢሳት ዜና–ነሐሴ 17/2009)ከአለማችን የሐገራት መሪዎች ለረዥም አመታት ስልጣን ላይ በመቆየት በሁለተኝነት የሚጠቀሱት የአንጎላው ፕሬዝደንት ጆሴ ኤድዋርዶ ዶሳንቶስ በሰላም ስልጣናቸውን ለመልቀቅ በወሰኑት መሰረት ርሳቸውን የሚተካ ምርጫ እየተካሄደ ይገኛል።

የገዢው ፓርቲ መከላከያ ሚኒስትር ምናልባትም የሀገሪቱን መንበረ ስልጣን ሳይረከቡ አይቀርም የሚል ቅድሚያ ግምት ተሰጥቷል።

የ28 ሚሊየን ህዝብ ሀገር የሆነችውን አንጎላን ለ38 አመታት የመሩት ጆሴ ኤድዋርዶ ዶሳንቶስ ለተጨማሪ የስልጣን ዘመን እንደማይወዳደሩ በማሳወቃቸው እርሳቸውን ለመተካት ዛሬ ምርጫ ተካሂዷል።
ፕሬዝዳንት ዶሳንቶስም በመራጭነት ተሳትፈዋል።

በገዢው ፓርቲ ኤም ፒ ኤል ኤ እንዲሁም በዋነኛው ተቃዋሚ ዩኒታና በፓርላማው አነስተኛ ድምጽ ባላቸው ሁለት እጩዎች መካከል የሚካሄደው ምርጫ አንጎላን እንደአውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ1979 ወዲህ ሌላ መሪ እንድታገኝ ያደርጋታል።

አንጎላን ከፖርቹጋል ቅኝ አገዛዝ ለማውጣት በተደረገው ትግል በግንባር ቀደምትነት ከተሳተፉት አንዱ የነበሩትና የነጻዋ አንጎላ የመጀመሪያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆሴ ኤድዋርዶ ዶሳንቶስ ነበሩ።
አንጎላ ነጻ ከወጣችበት እንደ አውሮፓውያኑ 1975 ጀምሮም ፕሬዝዳንት የነበሩት ኦጎስቲኖ ኒቶ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር መስከረም 10 1979 ሲሞቱ የአንጎላን የመሪነት መንበር የጨበጡት ጆሴ ኤድዋርዶ ዶሳንቶስ ናቸው።

ዶሳንቶስ ለ38 አመታት የዘለቁበትን መንበር በፈቃዳቸው በበቃኝ አሳልፈው በመስጠት በ74 አመታቸው የክብር ስንብት የሚያደርጉበት ምእራፍ ላይ ደርሰዋል።
እንደ አውሮፓውያኑ በ1969 ከቀድሞው ሶቭየት ህብረት በፔትሮሊየም ኢንጂነሪንግ ዲግሪ የተቀበሉትና በነዳጅ በበለጸገችው ሀገር ለ38 አመታት በሀገሪቱ መንበር ላይ የዘለቁት ኤድዋርዶ ዶሳንቶስ ከአለማችን መሪዎች ስልጣን ላይ በመቆየት በ2ተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

ስልጣን ላይ በመቆየት ከአለም መሪዎች ቀዳሚነቱን ይዘው አሁንም የቀጠሉት አፍሪካዊው የኢኳቶሪያል ጊኒ መሪ ቴዎድሮ ኦቢያንግ ምባሶጎ ናቸው።
ዶሳንቶስ ስልጣናቸውን ሲለቁ ሮበርት ሙጋቤ በ37 አመት ከ127 ቀናትን በመያዝ ቁጥር 2 ይሆናሉ።
የገዢው ፓርቲ መከላከያ ሚኒስትር ምናልባትም የሀገሪቱን መንበረ ስልጣን ሳይረከቡ አይቀርም የሚል ቅድሚያ ግምት ተሰጥቷል።

በሰላማዊ መንገድ በተካሄደው ምርጫም በርካታ አንጎላውያን መሳተፋቸውን ሮይተርስ በዘገባው አመልክቷል።